ትግራይ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ ሕግ ለማስከበር ከምትወስደው እርምጃ አንጻር የአፍሪካ አገራት ከጎኗ እንዲቆሙ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአፍሪካ አገራት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ የጠየቁት አገራቸው በግዛቷ ውስጥ ሕግን ለማስከበር በምትሞክርበት ጊዜ የተቀናጀ ዓለም አቀፍ ዘመቻ እንደገጠማት በማመልከት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለአፍሪካ ሕብረት የሠላምና የደኅንነት ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ንግግር ላይ ነው።
"ኢትዮጵያ በድንበሯ ውስጥ ሕግን ለማስከበር ስትንቀሳቀስ የተቀናጀ ዓለም አቀፍ የትችት ግፊት ውስጥ እያለፈች ባለበት በዚህ ወቅት አፍሪካውያን ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔን ደግፈው ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጥሪዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።
ጨምረውም በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ሕብረታቸውንና ድጋፋቸውን አሳይተዋል ላሏቸው ለአፍሪካ ሕብረትና አባል አገራቱ ምስጋና አቅርበዋል።
ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ህወሓት ላይ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲካሄድ ማዘዛቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መቀለን እንደተቆጣጠረ መግለጹን ተከትሎ እጅ አንሰጥም ያሉ የህወሓት አመራሮች እና አባላትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ዘመቻ ተከፍቷል።
በዚህ ወቅት በትግራይ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ ነው የሚሉ ክሶች እየተሰሙ ነው። መንግሥት እነዚህን ክሶች አጣጥሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአፍሪካ ሕብረት የሠላምና የደኅንነት ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ንግግር ላይ፣ በትግራይ ክልል ስለተከሰተው ግጭት በስፋትና በዝርዝር ሂደቱን ያብራሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት እያከናወነ ያለውን ዕርዳታ የማቅረብና የመልሶ ግንባታ ተግባሮችን አብራርተዋል።
በክልሉ ሆን ተብሎ ዜጎችን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ተይዘዋል የሚለው ክስ መሠረት የሌለውና አለመግባባትን ለማስፋፋት የታለመ ነው ብለዋል።
በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር ተያይዞ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶችን ሲያወጡ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ የሰብአዊና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመሆን ግልጽ ምርመራ እንዲያደርግ ለመተባበር መንግሥታቸው ፈቃደኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገርም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አክሱምን ጨምሮ በሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የራሱን ገለልተኛ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የሠላማና ደኅንነት ምክር ቤት 15 አባላት ያሉት በአህጉሪቱ ግጭቶችን ለመከላከልና መፍትሔ ለመስጠት እንዲሁም ግጭቶችን በተመለከተ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመ ቋሚ የሕብረቱ አካል ነው።
ከአራት ወራት በፊት በትግራይ ክልል በተከሰተው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር አስካሁን በውል ኤእታወቅም።
ነገር ግን ግጭቱን በመሸሽ ከ60 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ሲሰደዱ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደግሞ እዚያው በክልሉ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ የረድኤት ድርጅቶች ገልጸዋል።
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ግድያዎችና ከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች በመገናኛ ብዙሃንና አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂማን ራይትስ ዋችን በመሳሰሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በኩል በተከታታይ ሲወጡ መቆየታቸው ይታወሳል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ላይ በትግራይ ግጭት የተሳተፉ አካላት እንደ ጦር ወንጀልና በሰብአዊነት ላይ እንደተፈጸሙ ወንጀሎች ሊታዩ የሚችሉ ድርጊቶችን መፈጸማቸውን ሳይፈጽሙ እንዳልቀረ ገልጿል።
በዚህም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉትንና እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ሪፖርት የተደረጉ የጅምላ ግድያዎችን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ወሲባዊ ጥቃቶችን ለመመርመር እንዲችል ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ከትግራይ ክልል ግጭት ጋር በተያያዘ የተነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ግድያዎችን በተመለከተ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ከሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመሆን ምርመራ እያደረገ መሆኑን አመልክቶ፤ በምርመራው ላይ ተጨማሪ እርዳታ ካስፈለገ መንግሥት የውጭ አካላትን ሊጋብዝ እንደሚችል መግለጹ ይታወሳል።
መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል ውስጥ ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ በክልሉ ያጋጠሙ ግድያዎችናና ጾታዊ ጥቃቶችን በተመለከተ ሪፖርት አውጥቶ ነበር።















