ጃፓናዊው ቢሊየነር ወደ ጨረቃ አብራችሁኝ መጓዝ የምትፈልጉ ማመልከቻ አስገቡ አለ

ጃፓናዊው ቢሊየነር ያሳኩ ማኢዛዋ ወደ ጨረቃ አብረውኝ የሚጓዙ ስምንት ሰዎችን እፈልጋለሁ አለ

ያሳኩ ማኢዛዋ ወደ ጨረቃ የሚጓዘው በአሜሪካዊው ቢሊየነር ኤለን ማስክ ድርጅት በሚዘጋጀው የሕዋ ጉዞ ነው።

''ከተለያየ የማህብረሰብ ክፍል የሚመጡ ሰዎችን ነው የምፈልገው'' ብሏል በትዊተር ገጹ ላይ ባስተላለፈው የተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክት። ቢሊየነሩ ወደ ጨረቃ ለመሄድ የሚፈልጉ ሰዎች ሊያመለክቱ የሚችሉበትን የድረ-ገጽ አድራሻም አስቀምጧል።

ፍቃደኝነታቸውን በመግለጽ ወደ ጨረቃ ለመሄድ የሚመረጡ ሰዎች ወደ ጨረቃ ለሚደረገው ጉዞ ሙሉ ወጪያቸው እንደሚሸፈን ቢሊየነሩ አስታውቋል።

'ዲርሙን' ወይም በአማርኛ ውዷ ጨረቃ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ጉዞ በአውሮፓውያኑ 2023 እንደሚደረግ እቅድ ተይዞለታል።

ነገር ግን ወደ ጨረቃ መሄድ የፈለገ በሙሉ አይመረጥም። አመልካቾች ማሟላት የሚገባቸው በርካታ መስፈርቶች እንዳሉ ተገልጿል።

''በማንኛውም አይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ሰዎችን በማንኛውም ጊዜ ለመርዳት ዝግጁ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ነው የምፈልገው። በተጨማሪም በጨረቃ ላይ በሚኖረን ቆይታ የበረራ ቡድን አባላትን ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑ'' ብሏል።

አክሎም ''ሁሉንም የመንኩራኩሩን መቀመጫዎች ገዝቻቸዋለሁ። ስለዚህ በረራው ግላዊ ነጻነትን በጠበቀ መልኩ ነው የሚደረገው'' ብሏል።

ጃፓናዊው ቢሊየነር ያሳኩ በአልባሳት ኢንዱስትሪው እጅግ ስኬታማ የንግድ ሰው ሲሆን በተጨማሪም የተለያዩ የአርት ስራዎችን በመሰብሰብ ይታወቃል። እንደ ቢሊየነሩ ከሆነ መጀመሪያ ላይ ወደ ጨረቃ ሊወስድ ያሰበው አርቲስቶችን ነበር። ነገር ግን ሀሳቡን ቀይሮ ከመላው ዓለም የተወጣጡ ሰዎችን ወደ ጨረቃ መውሰድ የሚለውን ሀሳብ እንደመረጠ ገልጿል።

ባለፈው ዓመት ይሄው ቢሊየነር በአንድ ዘጋቢ ፊልም አማካይነት ወደ ጨረቃ አብራው የምትጓዝ የፍቅር አጋር እየፈለገ እንደሆነ አስታውቆ የነበረ ሲሆን ''የተቀላቀሉ ስሜቶች ስላስቸገሩኝ'' በማለት ትቶታል።

ያሳኩ ማኢዛዋ ወደ ጨረቃ ለሚደረገው ጉዞ ምን ያክል እንደከፈለ ይፋ አልተደረገም።