ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለዓለም ያስገኛቸው አስር ትሩፋቶች
በአንድ ዓመት ውስጥ ከ115 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የያዘውና ከ2.5 በላይ ሰዎችን ደግሞ ለሞት ዳረገውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመጣል ሳይንስ፣ ዕውቀትና ትብብር ተጣምረው ብዙ ታግለዋል፤ እየታገሉም ይገኛሉ።
ቫይረሱ አዲስ ዝርያ ማፍራቱን ተከትሎ በሚቀጥሉት ሳምንታትና ወራት ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት ቢያዳግትም አንድ ዓመት የሞላው ወረርሽኝ ብዙ አስተምሮናል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብዙዎችን ቢቀጥፍም ከዚህ በፊት በአዕምሯችን ውል ያላሉ በጎ ትሩፋቶችን አስገኝቷል ይላሉ ባለሙያዎች።
ከእዚህ ውስጥም እስቲ አስሩን ከኮቪድ-19 ትሩፋቶች እንመልከት።
1 - ኮቪድ-19 የወባን ማዕረግ መረከቡ
ከአንድ ዓመት በፊት ማለትም ስለወረርሽኙ መዘገብ ከጀመረ ከአንድ ወር በኋላ በሕክምና መጽሔቶች ላይ ከ164 በላይ ፅሑፎች ስለኮቪድ-19 ታትሞ ወጥቷል።
ከአንድ ዓመት በኋላ ዛሬ ስለወረርሽኙ የተፃፉ የጥናትና የምርምር ዘገባዎች ቁጥር በ600 እጥፍ ጨምሮ ከ100 ሺህ በላይ ሆኗል።
ይህን ማዕረግ ቀድሞ ይዞ ነበር ወባ ነበር። ዘንድሮ ለወትሮው አብዝተን ከምንሰማቸው የበሽታ ዘገባዎች በላይ ስለ ኮቪድ-19 በብዛት ይነገራል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ከወባ በላይ ስለኮቪድ-19 የበለጠ ዕውቀት አለ።
2 - ከ200 በላይ ክትባቶች
ከአንድ ዓመት በፊት ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ይረዳሉ ተብለው ጥናት ሲደረግባቸው የነበሩ ክትባቶች ቁጥር ስምንት ነበር።
ባዮሬንደር የተሰኘው ድርጅት እንደሚለው አሁን ከ195 በላይ ክትባቶች በተለያዩ የሂደት ደረጃ ላይ ሲሆኑ 71 ያህሉ ደግሞ በሙከራ ደረጃ ላይ ናቸው።
ፀረ-ኮሮናቫይረስ ክትባቶችን ለማምረት የወጣውን ወጪ፣ ትብብርና ጥናት ያክል ለሌሎች በሽታዎች ይህን የመሰለ ርብርብ አልተደረገም ይላሉ ባለሙያዎች።
በዚህ ጥናት ላይ ሕዝቡ፣ የግል ድርጅቶች፣ አጥኚዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ መድኃኒት አምራቾች፣ እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሳትፈዋል።
እርግጥ ነው አንዳንድ የጥናት ሂደቶች በእንጭጭ ቀርተዋል። ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅተ ያፀደቃቸው ደግሞ በርካታ ናቸው።
ፋይዘር/ባዮንቴክ፣ ሞደርና፣ አስታራዜኔካ/ኦክስፎርድ፣ ስፑትኒክ 5 እንዲሁም የቻይናው ሲኖፋርምና ጎል ተብለው የሚጠቀሱ ክትባቶች ናቸው።
ቢያንስ 20 ሌሎች ክትባቶች ደግሞ የሙከራ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ምናልባትም በሚቀጥሉት ሳምንታት አሊያም ወራት ውጤታቸው ተለይቶ ወደ ሥራ ሊገቡ ይችላሉ።
3 - የክትባቶች የጎንዮሽ ጉዳት አነስተኛ መሆን
የክትባቶች ትልቁ ደንቃራ በሳይንስ ቋንቋ አናፊላክሲስ ይባላል። ይህም የክትባቶቹ ጎንዮሽ ጉዳት ሲሆን ክትባት ከተወሰደ በኋላ ወዲያው የሚከሰት ሲሆን እስከሞት ሊያደርስ ይችላል።
አሜሪካ ውስጥ ክትባቱ በተሰጠበት የመጀመሪያው ወር ላይ የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው 17.5 ሚሊየን ክትባቶች ተሰጥዋል።
ከእነዚህ የፋይዘርና የሞደርና ክትባቶችን ከወሰዱ ሰዎች መካከል 66ቱ ብቻ ናቸው ይህ የጎንዮሽ ጉዳት የገጠማቸው።
ይህ በሚሊዮንኛ ሲሰላ ከአንድ ሚሊዮን ሰው 4 ብቻ ነው ማለት ነው። በመቶኛ ሲሰላ ደግሞ 0.0003 ይሆናል።
ከ66ቱ ሰዎች መካከል 21 ሰዎች ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸው ያውቃል። በዚህ የጎንዮሽ ጉዳት ምክንያት እስከዛሬ ድረስ የሞተ ሰው የለም።
የዚህ ጥናት ውጤት ለጊዜውም ቢሆን የሚጠቁመው ክትባቶች ከጉዳታቸው ጥቅማቸው በእጅጉ እንደሚያመዝን መሆኑ ነው።
በተለይ ደግሞ የሞደርና ክትባት ከሌሎቹ በላቀ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንደሆነ ተነግሯል።
4 - ክትባቶች ውጤታማ ናቸው
እስራኤል በርካታውን ዜጎቿን በመከተብ ከዓለም ቀዳሚ ናት።
እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ ከ3.67 በላይ እስራኤላዊያን የፋይዘርን የመጀመሪያ ዙር ክትባት ወስደዋል።
ይህ ከአገሪቱ ሕዝብ 40 በመቶውን የሚይዝ ነው። ከ28 በመቶ በላዩ ደግሞ ሁለተኛውን ዙር ክትባት ወስደዋል።
ከ60 ዓመት በላይ ከሆናቸው ዜጎቿ መካከል ደግሞ 80 በመቶው ተከትበዋል።
የክትባቶቹ የመጀመሪያ ዙር ውጤት እንደሚያሳየው ክትባቶች እስካሁን ድረስ ባለው ጥናት መሠረት ውጤታማ መሆናቸውን ነው።
በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም ከጊዜ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፤ በለተይ ደግሞ ዕድሜያቸውን 60ና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ።
ሁለቱንም ዙር ክትባት ከወሰዱ 523 ሺህ እስራኤላዊያን መካከል 544 ሰዎች ላይ ብቻ ነው ኮቪድ-19 የተገኘው። እስካሁን ድረስ የተመዘገበ ሞት ግን የለም።
ነገር ግን የክትባቱን ውጤታማነት ለማየት የግድ ወደ እስራኤል መሻገር አይጠበቅብንም።
የክትባቶችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በአዛውንቶች ማቆያ ማዕከላት የሚኖሩና አሁን ክትባቱ የደረሳቸውን ሰዎች ቁጥር ማየት ይቻላል።
በአብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት ያሉ በዕድሜ የገፉ ሰዎች አሁን ክትባቱን ካገኙ በኋላ የመያዝ ዕድላቸውና የሞት ቁጥር በእጅጉ እየቀነሰ ነው።
5 - በክትባት ላይ መተማመን መጨመር
በዓለም ዙሪያ እስካሁን ድረስ ከ160 ሚሊዮን በላይ ብልቃጦች ጥቅም ላይ ውለዋል።
የዚያኑ ያህል ሰዎች በክትባት ላይ ያላቸው መተማንም ከዕለት ዕለት እየጨመረ ነው።
ለምሳሌ በአውሮፓ፣ እስያና አውስትራሊያ አገራት የሚኖሩ 13 ሺህ 500 ሰዎችን መሠረት አድርጎ አንድ ጥናት ተሠርቷል።
ጥናቱ ከኅዳር እስከ ጥር ባለው ጊዜ የተሠራ ነው። ኅዳር ላይ አገራት ክትባት መስጠት ከመጀመራቸው በፊት 40 በመቶ ሰዎች ብቻ ነበሩ በክትባቱ ሙሉ እምነት የነበራቸው።
ነገር ግን ጥር ላይ ከ50 በመቶ በላይ ሰዎች በክትባቶች ላይ ያላቸው እምነት ሲጨምር ክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳት አለው ብለው የሚያምኑ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ቀንሷል።
በዩናይት ኪንግደም ካሉ ሰዎች በተሰበሰበ መረጃ መሠረት ከ78 በመቶ በላይ ሰዎች ክትባቱን ለመውሰድ ዝግጁ ናቸው።
6 - በሽታን የመከላከል አቅም ከ8 ወራት በላይ አይዘልቅም
አንድ ሰው በኮቪድ-19 ተይዞ ከተሻለው በኋላ የሚኖረው የመከላከል አቅም ምን ያህል ነው? የሚለውን ለመለየት የተሠሩ ጥናቶች ሙሉ ገፅታውን አያሳዩም።
የበሽታ የመከላከል አቅም ምን ያህል ይቆያል የሚለውን መለየት እጅግ ጠቃሚ ነው። ይህ የክትባት የመከላከል አቅምን ለመለየትም ያስችላል።
ምንም እንኳ የእያንዳንዱ ሰው በሽታን የመከላከል አቅም ቢለያይም በበርካታ አገራት የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቆይታው ከ6 አስከ 8 ወራት መሆኑን ነው።
ይህ የመከላከል አቅም ቆይታ ሰዎች በበሽታው እጅጉን ተጠቁም አልተጠቁም ተመሳሳይ ነው።
7 - በጣም ለተጎዱ ሰዎች መድኃኒት ፍለጋ
ኮቪድ-19 ከሳንባ ምች [ኒሞኒያ] በላይ የከፋ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
ምንም እንኳ ኮሮናቫይረስን ነጥሎ የሚያጠቃ መድኃኒት ባይኖርም በጣም ለተጎዱ ሰዎች ከሞት የሚታደጉ መድኃኒቶችን ደባልቆ መስጠት ተችሏል።
እኒህን መድኃኒቶች ደባልቆ መስጠት ያለውን ሚና የሚለዩ ከ400 በላይ ጥናቶች የሙከራ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በየቀኑ የኮሮናቫይረስ በሽታ ለጠናባቸው ሰዎች የሚሆኑ መድኃኒቶች ቅመማ ከጊዜ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።
8 - ጉንፋን መጥፋት
ኮሮናቫይረስ ዓለምን ማዳረስ በጀመረበት ወቅት የነበረው አንዱ ፍራቻ በክረምት ወራት ከሚነሱ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ጋር እንዴት ያደርገናል የሚለው ነበር።
እንደ ጉንፋን፣ ኢንፍሉዌንዛና አስም የመሳሰሉ የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቁ በሽታዎች ወደ ሳንባ ምችና ብሮንካይትስ ሊያመሩ ይችላሉ።
እነዚህ በሽታዎች በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች በተለይ ደግሞ ተጋላጭ በሚባሉቱ አገራት እስከ ሞት የሚያደርሱ ናቸው።
በኢንፍሉዌንዛና በኮሮናቫይረስ በአንድ ጊዜ የተጠቁ ሰዎች የመሞት ዕድል በኮቪድ-19 ብቻ ከተያዙት ላቅ ያለ ነው። በተለይ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ70 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ አደጋው ይጨምራል።
ነገር ግን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎችን መጠቀም እንደ ጉንፋን ያሉ በሽታዎች እንዲቀንሱ ትልቅ ምክንያት ሆኗል።
መልካሙ ዜና በክረምት ወራት የሚከሰቱ በሽታዎች ጉዳት እንደሌላው ጊዜ አለመሆን ነው። ነገር ግን ይህ ጉዳይ በቀጣዩ ዓመት ክረምት ተመልሶ ሊመጣ እንደሚችል ይገመታል።
ኢንፍሉዌንዛ ኮሮናቫይረስ በባሕሪ በጣም የተለያዩ በሽታዎች መሆናቸውን ልብ ማለት ያሻል።
9 - የበሽታውን ዕድገት በየደቂቃው መከታተል እንችላለን
አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ጥቅም ላይ እየዋሉ ባሉ ክትባቶች ላይ ያለው ኃያልነት እስካሁን በውል አልተረጋገጠም።
ቢሆንም አንድ መልካም ዜና አለ። አሁን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ላይ እያንዳንዱን ለውጥ በቅርበት መከታተል ይቻላል።
ሳይንቲስቶች የበሽታውን ዕድገት የሚያጠኑበትን መንገድ አዳብረዋል።
ጥናቶቹ ካለፈው ዓመት የካቲት እስካሁድ ድረስ ያለውን የበሽታውን ዕድገት ከሥር ከሥሩ የሚከታተሉ ናቸው።
እኒህ ጥናቶች የበሽታውን አካሄድ አጥንቶ መፍትሄ ለማበጀት ይረዳሉ።
የአንድን ወረርሽኝ እያንዳንዱ ዕድገትና ለውጥ በየደቂቃው ማጥናት የተቻለው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
10 - የወረርሽኙ መቀዛቀዝ
ተደጋግሞ እንደተጠቀሰው የኮሮናቫይረስ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለው አሁንም እርግጠኛ መልስ አልተገኘለትም።
ነገር ግን እስካሁን የነበረውን አካሄድ በማየት በየጊዜ የወረርሽኙ ማዕበሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም። ቢሆንም ተፅዕኗቸው ከዚህ በፊት ከነበረው ዝቅ እያለ የሚመጣ ነው።
አሁን እንደ መልካም ዜና እየተቆጠረ ያለው ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዚህ በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር መቀዛቀዝ ማሳየቱ ነው።
ለዚህ እንደምክንያት ከሚጠቀሱ ነገሮች መካከል አንደኛው በሽታውን የመከላከል አቅም መዳበር ነው። ለመከላከል አቅም አንዱ አጋዥ መሣሪያ ደግሞ ክትባት ነው።
ይህም የሽታውን መስፋፋት ለመግታት ትልቅ ተስፋን ሰጥቷል።