ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእነ አቶ ጃዋር የሕክምና ጉዳይ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ይግባኝን ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ሰዎች የሕክምና ጉዳይን በማስመልከት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ በመረጡት የግል ሃኪም እና የግል ሕክምና ጣቢያ እንዲታከሙ መፍቀዱን በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ ነበር።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቤቱታን ውድቅ ያደረገ ሲሆን፤ ተከሳሾች ግን በመረጡት ሃኪም የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ያለባቸው በግል ሆስፒታል ሳይሆን ተከሳሾች ታስረው በሚገኙበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲሆን ትዕዛዝ መስጠቱን ከእነ አቶ ጃዋር ጠበቆች መካከል አቶ ሚኪያስ ቡልቻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ እና ሐምዛ አዳነን ጨምሮ ሌሎች በእነ አቶ ጃዋር የክስ መዝገብ ውስጥ የሚገኙ ተከሳሾች ከ25 ቀናት በላይ በረሃ አድማ ላይ እንደሚገኙ ጠበቆቻቸው ይናገራሉ።
ተከሳሾቹ እያደረጉት ባለው የረሃብ አድማ ምክንያት የቅርብ የጤና ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው የተከሳሾች የግል ሃኪም ዶ/ር ኢሊሊ ጀማል ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ተከሳሾች 'ለደህንነታችን እንሰጋለን' በማለት በመንግሥት የሕክምና አገልግሎት መስጫ ስፍራ ለመታከም ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
የተከሳሽ ጠበቆች እንደሚሉት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ በግል የጤና ተቋም እንዳይታከሙ የተከራከረው የተከሳሾችን ደህንነት በግል ሆስፒታል ማረጋገጥ አይቻልም በሚል ነው።
የዛሬው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ "የላንድ ማርክ ሃኪሞች ተደራጅተው ተከሳሾች ባሉበት በመምጣት ሕክምና እንዲሰጣቸው ነው" በማለት ጠበቃው አቶ ሚኪያስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ፍርድ ቤቱ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቤቱታ የሕግ መሠረት የለውም ብሎ ውድቅ ካደረገ በኋላ ተከሳሾች ማረሚያ ቤት ሆነው ይታከሙ መባሉ እርስ በእርሱ የሚጣረስ ነው" በማለት የተከሳሽ ጠበቆች በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ደስተኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
ጠቃው እንደሚሉት ደንበኞቻቸው ሆስፒታል ተኝተው መታከም የሚያስፈልጋቸው ከሆነ፣ የሆስቲታል ማሸኖች ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ እንዲሁም በጤና ባለሙያ የቅርብ ክትትል ቢያስፈልጋቸው በማረሚያ ቤት ሆነው መታከማቸው ይህን ስለማያሟላ፤ አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤቱ መልሰው እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም እነ አቶ ጃዋር የረሃብ አድማውን እንዲያቆሙ በሃይማኖት አባቶች እና ፖለቲከኞች ቢጠየቁም ፍቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው ይታወሳል።
ከእነ አቶ ጃዋር ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ከድር ቡሎ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም ጠበቆች እና የቤተሰብ አባላት ምግብ እንዲበሉ ሲጠይቋቸው ቢቆዩም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
የረሃብ አድማ ለምን?
እነ አቶ ጃዋር መሐመድ የረሃብ አድማውን እያደረጉ ያሉት በፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት እና እስር፣ እነሱን ለመጠየቅና የችሎት ሂደታቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ መሆኑን ጠበቆቻቸው ይናገራሉ።
እነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ እጃችሁ አለበት ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የረሃብ አድማው ተከሳሾችን የከፋ አደጋ ላይ እንዳይጥል የቅርብ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ አስነብቧል።