አንደኛው ክንፉ በአየር ላይ የተቦደሰው አውሮፕላን በሰላም አረፈ

የቦይንግ ንብረት የሆነው አውሮፕላን በአንደኛው ሞተር ላይ በደረሰበት እክል ምክንያት አካላቱን መኖሪያ ቤቶች መጣሉ ተሰምቷል።

ቦይንግ 777 የሆነው አውሮፕላን 231 መንገደኞች ያሳፈረ ሲሆን በተጨማሪ 10 የአየር መንገዱ ሠራተኞች ነበሩ።

ምንም እንኳ አውሮፕላኑ በደረሰበት እክል ምክንያት አካላቱ እየተቦዳደሱ ዴንቨር አካባቢ ያሉ መኖሪያ ቤቶች ላይ ቢያርፉም ተመልሶ በሰላም ማረፍ ችሏል።

አውሮፕላኑ በደረሰበት አደጋ ምክንያት ምንም ዓይነት ጉዳት ሰው ላይ አለመድረሱ ተዘግቧል።

የብሩምፊልድ ፖሊስ ከአውሮፕላኑ የወዳደቁ ናቸው የተባሉ የአንደኛው ሞተር ስብርባሪዎች ከመኖሪያ ቤቶች አቅራቢያ ማግኘቱን በፎቶ ማስረጃ አረጋግጧል።

ተሳፋሪዎች ልክ አውሮፕላኑ እንደተነሳ 'ከባድ ፍንዳታ' መስማታቸውን ተናግረዋል።

የበረራ ቁጥሩ 328 የሆነው ይህ አውሮፕላን የዩናይትድ ኤርላይንስ ንብረት ነው።

አውሮፕላኑ ከዴንቨር አውሮፕላኑ ማረፊያ ወደ ሆኖሉሉ [ሁዋይ] እየበረረ ሳለ ነው የቀኝ ክንፍ ሞተሩ ላይ አደጋ ያጋጠመው ሲል የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር አሳውቋል።

ኤፒ የዜና ወኪል ያነጋገረው አንድ ተሳፋሪ ከባድ ፍንዳታ የተሰማው የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ መልዕክት እያስተላለፈ ሳለ ነው ብሏል።

"አውሮፕላኑ በጣም መንቀጥቀጥ ጀመረ፤ ከዚያ የምንበርበት ከፍታ ትተን ወደታች መምዘግዘግ ጀመርን" ሲል ነው ተሳፋሪው ሁኔታውን የገለፀው።

ተሳፋሪው አክሎ ምናልባት አደጋ ቢከሰት መለየት እንዲችሉ እሱና ባለቤቱ መታወቂያ ወረቀታቸውን በኪሳቸው እንዳኖሩ ተናግሯል።

በይነ መረብ ላይ የተለጠፉ ፎቶዎች እንደሚያሳዩት እክል ከገጠመበት ክንፍ ላይ ጭስ ሲወጣ ነበር።

አንድ አውሮፕላኑ ውስጥ የነበረ ተሳፋሪ የቀረፀው ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው አንደኛው ሞተር በእሳት ከተያያዘ በኋላ ተሰብሮ ወደታች ተምዘግዝጓል።

ሲኤንኤን ያናገረው አንድ የአካባቢው ነዋሪ የአውሮፕላኑ ስባሪ ከሰማይ ወደታች ሲወድቅ አይቶ ልጆቹን ከለላ ፍለጋ ሲሯሯጥ እንደነበር ተናግሯል።

አደጋው የተከሰተው በሃገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ቅዳሜ ከሰዓት 7 ሰዓት አካባቢ ነው።

የብሉምፊልድ ፖሊስ ነዋሪዎች የአውሮፕላኑን ስብርባሪ ከቦታው እንዳያነሱ አሳስቧል።

የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደርና ብሔራዊው የትራንስፖርቴሽን ሴፍቲ ቦርድ አደጋውን እንደሚያጣሩ ተነግሯል።