ሕንድና ፓኪስታንን ያቀራረበው የአምስት ሰከንድ ቪዲዮ

የፎቶው ባለመብት, DANANEERR
ለአምስት ሰከንዶች የሚቆይ ተንቀሳቃሽ ምስል የማይታሰበውን ነገር ማድረግ ችሏል። ተንቀሳቃሽ ምስሉ የሕንድና ፓኪስታን ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን አንድ ላይ እንዳመጣ ተገልጿል።
ዳናኒር ሞቢን የተባለችው ፓኪስታናዊት የተንቀሳቃሽ ምስል ባለሙያ ኢንስታግራም ላይ የራሷን ቪዲዮ የለቀቀችው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር። ነገር ግን በአንድ ምሽት ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በሁለቱም አገራት ታዋቂና ተወዳጅ ሰው እሆናለሁ ብላ አላሰበችም ነበር።
ይህች ግለሰብ የለቀቀችው ምን አይነት ቪዲዮ ቢሆን ነው? ብላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ።
ቪዲዮው ምንም የተለየ ነገር የለውም ትላለች ሞቢን። ''ይህ የእኛ መኪና ነው፤ እኛም እዚሁ ነን፤ ይሄ ደግሞ የጭፈራ ዝጅግታችን ነው'' ብቻ ነው ያልኩት ትላለች። በቪዲዮው ላይ ጥቂት ወጣቶች ተሰብስበው ሲዝናኑም ይታያል።
ዋናው ነገር ያለው እዛ ጋር ነው። በቅርብ ሳምንታት ሞትና ሀዘን ብቻ ለሚሰማባቸው ሁለቱ አገራት ሰዎች ደስ ብሏለቸው ሲዝናኑና ጥሩ ጊዜ ሲያሳልፉ ማየት በርካቶችን አስደስቷል።
በተለይ ደግሞ ለበርካታ አስርት ዓመታት የቆየው የሁለቱ አገራት ደም አፋሳሽ ግጭትን ተከትሎ ዜጎች እንዲህ ባለ ሁኔታ በአንድ ጉዳይ ላይ ሲስማሙ አይታይም።
''በድንበሩ አካባቢ ደስታና ጥሩ ጊዜ ከሰዎች ጋር እንደማሳለፍ የመሰለ ምን ነገር አለ። ዓለም በክፍፍልና በችግር በተሞላችበት ወቅት ደስታን መካፈልን የመሰለ ነገር የለም'' ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።
''በለቀቅኩት ቪዲዮ ምክንያት ጎረቤቶቼ (ሕንዳውያን) እና እኔ በአንድ ላይ በመደሰታችን ተገርሜያለው'' ብላለች።
ዳናኒር ሞቢን የ19 ዓመት ወጣት ስትሆን በኢንስታግራም ላይ ታዋቂ ነች። ከፓኪስታኗ ሰሜናዊ ከተማ ፔሽዋር ነው የመጣችው። የምትለቃቸው ቪዲዮዎች አብዛኛውን ጊዜ ፋሽን እና ሜካፕ ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ከቪዲዮው በታች ባስቀመጠቸው ጽሁፍ ላይ 'በተራሮች ወደተከበበችው ሰሜናዊት ፓኪስታን መጥታችሁ የእረፍት ጊዜያችሁን አሳልፉ' የሚል መልዕክትም አስተላልፋለች።
ይህን ተንቀሳቃሽ ምስል የተመለከቱ ሌሎች ታዋቂ ፓኪስታናውያንም ቪዲዮውን በድጋሚ በመስራትና አስቂኝ ነገሮችን በመጨመር እንዲሁም ወደ ሌላኛው ማህበራዊ ሚዲያ ትዊተር በመውሰድ ይበልጥ ታዋቂ አደረጓት።
ወዲያውም በርካታ ታዋቂ ፊልም ሰሪዎችና ክሪኬት ተጫዋቾች ይቀባበሉት ጀመር። የፓኪስታን ክሪኬት ቦርድም ቢሆን የአገሪቱ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ቪዲዮውን በድጋሚ ሰርተው የሚታዩበትን ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አጋርቷል።
በመቀጠል ደግሞ አንድ ታዋቂ የሕንድ ዲጄ ቪዲዮውን በመጠቀም የሰራው ሙዚቃ የ19 ዓመቷ ዳናኒር ሞቢን ከፓኪስታን አልፋ በሕንድም ታዋቂ እንድትሆን አድርጓታል።












