የአገረሰብ ሙዚቃ ንግሥት ዶሊ ፓርተን ሐውልት እንዳይቆምልኝ አለች

በአሜሪካ የአገረሰብ ሙዚቃ ታሪክ ንግሥት ተደርጋ የምትታየው ዶሊ ፓርተን የቴነሲ ግዛት ለእርሷ ክብር ሐውልት ሊያቆም የያዘውን ሐሳብ ለጊዜው ውድቅ እንዲያደርገው ጠየቀች፡፡

የቴነሲ ግዛት ሕግ አውጪዎች ለሷ በናሽቪል ስቴት ካፒቶል የመንግሥት ሕንጻ ቅጥር ውስጥ ሐውልት እንዲቆም ያቀረቡትን ረቂቅ ድጋሚ እንዲያጤኑት ጠይቃለች፡፡

‹9 ቱ 5› ዘፈን ባለቤት ዶሊ በትዊተር ሰሌዳዋ እንደጻፈችው አሁን ለሷ ሐውልት የሚቆምበት ጊዜ አይደለም፡፡

‹አሁን በዓለማችን ላይ እየሆነ ካለው ደስ የማይል ሁኔታ አንጻር ለኔ በዚህ ጊዜ ስለ ሐውልት ማቆም ማውራት ስሜት አይሰጥም›› ብላለች ዶሊ፡፡

የአገረ ሰብ ሙዚቃ ንግሥት ዶሊ አሁን 75 ዓመቷ ነው፡፡

ሐውልት ልታቆሙልኝ ስላሰባችሁ እጅግ ክብር ተሰምቶኛል ብላለች፡፡

‹‹ነገር ግን ያ እንዲሆን የምመኘው ከብዙ ዓመታት በኋላ፣ ወይም እኔ ከሞትኩ በኋላ፣ ይገባታል ብላችሁ ካሰባችሁ ብቻ ቢሆን ነው የምመርጠው፡፡ ያን ጊዜ በካፒቶል ሂል እንደ አንዲት የቴነሲ ተወላጅ ደስታዬ ወደር አይኖረውም›› ብላለች፡፡

ባለፈው ኅዳር የአገረ ሰብ ሙዚቃ ንግሥት ዶሊ ለኮቪድ 19 ምርምር የሚሆን 1 ሚሊዮን ዶላር ለግሳ ነበር፡፡

ልገሳው በናሽቪል ቫንደርቢለት ዩኒቨርስቲ ለሚደረገው ጥናትና ምርምር የሚውል ነው፡፡ ይህ ማዕከል የሞደርና ክትባት ከሚሞከርባቸው ተቋማት አንዱ ነው፡፡

ሞደርና የኮቪድ ክትባት 95 ከመቶ ያህል ፈዋሽነቱ መረጋገጡ ይታወሳል፡፡

በዚህ ወር መጀመርያ ዶሊ ይፋ እንዳደረገችው በአሜሪካ ትልቁን የክብር ሽልማት እንድትቀበል በትራምፕ 2 ጊዜ ተጠይቃ ውድቅ አድርጋለች፡፡

ይህ ሽልማት ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትልቅ ተግባር ለፈጸሙ የሚበረከት ሲሆን የአሜሪካ ፕሬዝዳንሻል የነጻነት ሜዳሊያ ተብሎ ይጠራል፡፡

ሽልማቱን ለመቀበል ፍቃደኛ ያልሆነችው ባለቤቷ ታሞ ስለነበረ ወደ ዋሺንግተን ለመጓዝ ባለመፍቀዷ ነው፡፡ ዶሊ ለ5 አሥርታት በትዳር የጸናች ናት፡፡

ከሙዚቃ ባሻገር በሲኒማ ተሳትፎዋ የምትታወቅ ሲሆን 9 ቱ 5 ፊልም ተዋናይ ስትሆን በዚሁ ርዕስም ሙዚቃ ተጫውታለች፡፡

ዶሊ ፓርተን በሕይወት ዘመኗ ፖለቲካ ውስጥ ገብታ አታውቅም፡፡ ፖለቲካዊ አስተያየት መስጠትም አትወድም፡፡ ሆኖም ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ለጥቁሮች መብት እንቅስቃሴ (ብላክ ላይቭስ ማተር) ድጋፏን ሰጥታ አነጋጋሪ ሆና ነበር፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠይቃ ለቢልቦርድ መጋዚን ስትመልስ ‹‹የኛ የነጮች ሕይወት ብቻ ነው ዋጋ ያለው የሚመስልህ? ግድ የሚሰጥህ የነጮች ጉዳይ ሲሆን ከሆነ ትክክል አይደለም›› ብላ መልሳለች፡፡

ዶሊ ፓርተን ሕይወቷን በሙሉ ለጋስ በመሆን በአሜሪካዊያን ዘንድ ትታወቃለች፡፡ ዶሊውድ ፋውንዴሽን ለበርካታ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት ስመ ጥር ነው፡፡ በልጅነቷ በአስቸጋሪ ድህነት እንዳደገች ዶሊ ትናገራለች፡፡

ዶሊ ፓርተን ‹‹አይ ዊል ኦልዎይስ ላቭ ዩ› እና ‹ጆሊን› በሚለው ሙዚቃዎቿ በኛም አገር ይበልጥ ትታወቃለች፡፡

ዶሊ የ9 ግራሚ ሽልማቶች አሸናፊ ናት፡፡

ዶሊ ከሌላኛው የአገረሰብ ሙዚቃ አቀንቃኝ ኬኒ ሮጀርስ የተጫወተችው ሙዚቃ በታሪክ በጥምረት ተዘፍነው እጅግ ተወዳጅነት ካገኙ ሙዚቃዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

‹አይላንድስ ኢን ዘ ስትሪም› የተሰኘው የጥምረት ሙዚቃ በዶሊና በኬኒ ሮጀርስ የተቀነቀነ ዘመን አይሽሬ ሙዚቃ ተደርጎ ዛሬም ድረስ ይወደዳል፡፡