አረብ ኤምሬቶች ፡ የተባበሩት መንግሥታት በአባቷ ስለታገተችውን ልዕልት ሊነጋገር ነው

የተባበሩት መንግሥታት የዱባዩ መሪ ልጅ የሆነችው ልዕልት ላቲፋ መታገቷን በተመለከተ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር እንደሚነጋገር አስታወቀ።

ልዕልቷ እአአ በ2018 አገሪቱን ለቃ ለመውጣት ከሞከረች በኋላ አባቷ ዱባይ ውስጥ እንዳገቷት የሚያሳይና በሚስጥር የተቀዳ ቪድዮ ለቢቢሲ ልካለች። ልዕልቷ ለሕይወቷ እንደምትሰጋ በቪድዮው ገልጻለች።

ቪድዮው ከተለቀቀ በኋላ ጉዳዩን የተባበሩት መንግሥታት እንዲያመረምረው ተጠይቋል። የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶምኒክ ራብ "ቪድዮው ይረብሻል። በጣም አሳስቦናል" ብለዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም በጉዳዩ ላይ ተመድ የሚያደርገውን ምርመራ በቅርብ እንደምትከታተልም ተናግረዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር፤ ልዕልቷን በተመለከተ በቅርቡ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ ሩፔት ኮቪል "የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ማብራሪያ እንጠይቃለን። ከዚያም ቪድዮው ተመርምሮ ሌሎች የድርጅቱ አባሎችም ይካተታሉ" ብለዋል።

የልዕልት ላቲፋ አባት ሼክ መሐመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም የዱባይ መሪና የኤምሬቶች ምክትል ፕሬዘዳት ሲሆኑ፤ ከዓለም ሀብታሞች መካከል ይጠቀሳሉ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት ሴቶችን እንደሚጨቁን ይናገራሉ። ልዕልት ላቲፋ በጓደኞቿ እገዛ ከዱባይ ለማምለጥ የሞከረችውም ለዚህ ነው።

"መኪና መንዳት አልችልም። ከዱባይ መውጣት አይፈቀድልምኝም" ስትል ከዱባይ ለማምለጥ ከመሞከሯ በፊት በቀረጸችው ቪድዮ ተናግራለች።

ለማምለጥ ሞክራ በቀናት ውስጥ በሕንድ ውቅያኖስ መርከብ ውስጥ ተይዛ ወደ ዱባይ ተመልሳለች። አባቷ የእሷን ፍላጎት ለመጠበቅ እየሞከርኩ ነው ሲሉ፤ ቤተሰቧም ከእነሱ ጋር መሆን እንዳለባት ተናግረው ነበር።

ኤምሬቶችና የሴቶች መብት ጥሰት

የልዕልት ላቲፋ ጉዳይ የመላው ዓለም መነጋገሪያ ከመሆኑ ባሻገር በኤምሬቶች ያለውን የሴቶች ጭቆና አጋልጧል።

የዓለም የምጣኔ ሀብት ፎረም በ2020 ባወጣው የጾታ እኩልነት ጥሰት ሪፓርት፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከሰሜን አፍሪካ አገሮች ሁለተኛውን ደረጃ ይዟል።

ከእስራኤል ውጪ ያሉት አገራት በቀጠናው የጾታ እኩልነትን ባለማክበር ይታወቃሉ። በዓለም የጾታ እኩልነት ዝርዝር ውስጥ ዝቅተኛውን ደረጃም ይዘዋል።

የሴቶች ሕይወት በወንድ ቤተሰቦቻቸው ወይም የትዳር አጋራቸው ቁጥጥር ሥር ነው። ለማግባት ወይም ለመፋታትም የወንዶች ይሁንታ ያስፈልጋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሕጉ ላይ አንጻራዊ መሻሻል ቢታይም፤ አሁን ሥርዓቱ ጨቋኝ ነው።

ለምሳሌ የአገሪቱ ሕግ የቤት ውስጥ ጥቃትን እንደ ጥፋት አያይም ነበር። 2016 ላይ ግን ይህ ተቀይሯል።

ሕጉ ሴቶች ባላቸውን ማክበር "ግዴታቸው ነው" ይል የነበረ ሲሆን፤ 2019 ላይ ይህ አንቀጽ ተቀይሯል።

ሆኖም ግን ሕጉ የቤት ውስጥ ጥቃት የሚለው፤ አንድ ሰው የሚያደርሰው ጥቃት እንደ አስተዳዳሪ ከተፈቀደለት ሲያልፍ ብቻ ነው ይላል።

ይህ ማለትም ዳኞች የደረሰውን የጥቃት መጠን መዝነው "ከተፈቀደው በላይ ነው ወይስ በታች" ሲሉ ይወስናሉ ማለት ነው።

ሼክ መሐመድ ልጃቸው ልዕልት ላቲፋን በተመለከተ ሲተቹ ነበር። የልዕልቷ እንጀራ እናት ልዕልት ሀያ ቢንት አልሁሴን ከሁለት ልጆቻቸው ጋር በ2019 ወደ ለንደን መሸሻቸውም ይታወሳል።