ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በባንግላዴሽ ጦማሪውን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉት በሞት ተቀጡ
የባንግላዴሹ ፍርድ ቤት ጦማሪውን በአሰቃቂ ሁኔታ በቆንጨራ ገድለዋል ያላቸውን አምስት ግለሰቦች በሞት ሲቀጣ አንደኛውን ደግሞ የእድሜ ልክ እስራት ፈርዶበታል።
ጦማሪው አቭጂት ሮይ የተገደለው ከስድስት አመታት በፊት ድሃካ በምትባል ቦታ ነው።
መኖሪያውን በአሜሪካ አድርጎ የነበረው የባንግላዴሹ ጦማሪ በመዲናዋ ድሃካ ከመፅሃፍ ትዕይንት ቆይቶ ሲወጣ ነው በቆንጨራ የገደሉት ተብሏል።
ኢ-አማኒ ነው የተባለው አቭጂት እምነትን አስመርኩዞ በሚፅፋቸው ጉዳዮች አክራሪዎችን አስቆጥቷል ተብሏል። ሙክቶ ሞና (ነፃ ሃሳብ) የሚባል ድረ ገፅ የነበረው ሲሆን በፅሁፎቹም በርካታ የግድያ ማስፈራሪያዎች ደርሰውታል። ጦማሪው በሙያው መሃንዲስ እንደሆነም ተነግሯል።
በተገደለበት ወቅት ባለቤቱ ራፊዳ አህመድ አብራው የነበረች ሲሆን እሷም በከፍተኛ ሁኔታ እንደቆሰለች ተገልጿል። ድሃካ ዩኒቨርስቲ ግቢን ለቀው በወጡበት ወቅት ነው ጥቃቱ የደረሰባቸው ተብሏል።
ጥቃቱን ያደረሱት ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አለው የተባለና በአገሪቱም እንዳይንቀሳቀስ የታገደው አንሳር አል ኢስላም ቡድን መሆኑን ከፍርድ ቤቱ ከተሰሙት መረጃዎች ተገኝቷል።
ጥቃቱን መርተዋል የተባለው የጦር ጄኔራል ሰይድ ዚያውል ሃኬን ጨምሮ ሌላ ግለሰብ በሌሉበት ነው ሞት የተፈረደባቸው።
የጦር ጄኔራሉን ጨምሮ አክራም ሁሴይን የተባለ ሌላ ግለሰብ በመንግሥት ለጦማሪው ግድያ በባንግላዴሽ መንግሥት እየታደኑ ነው ተብሏል። ፍርድ ቤቱ በአጠቃላይ አምስቱ በስቅላት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል።
ስድስተኛው ግለሰብ ሻፊዩር ራህማን ፋራቢ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።
በአውሮፓውያኑ 2016 የጥቃቱ ሌላኛው መሪ ነው ፖሊስ ያለው ሻሪፍ የተባለ ተጠርጣሪ በመዲናዋ በነበረ የተኩስ ልውውጥ እንደተገደለም ፖሊስ አስታውቋል።
ከጦማሪው በተጨማሪ ሌሎች የመብት ተሟጋቾችንና ፀሃፊዎች ግድያ ጀርባ ይኼ ቡድን እንዳለ ፖሊስ አስታውቋል።
ከአውሮፓውያኑ 2013-2016 ውስጥ ባለው ወቅት በአልቃይዳና አይኤስ ጋር ግንኙነት አለው የተባለ ቡድን በርካታ ግድያዎችን ፈፅሟል።
ከነዚህም ውስጥ አንዱ በዳህካ ሆሊ አርቲሳን በሚባል ካፌ አንድ ታጣቂ ገብቶ 20 ሰዎችን ገድሏል። ካፌው ከውጭ አገራት በመጡ ዜጎች የሚዘወተር ነበር የተባለ ሲሆን በርካታዎቹ የሞቱት የውጭ አገራት ዜጎች እንደሆነም ተገልጿል።