ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዲሞክራቲክ ኮንጎ በጀልባ ላይ በደረሰ አደጋ ቢያንስ 60 ሰዎች ሞተዋል ተባለ
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አንዲት ጀልባ ወንዝ ላይ ባጋጠማት አደጋ ቢያንስ 60 ሰዎች ሰጥመው መሞታቸው ተሰምቷል።
በኮንጎ ወንዝ ላይ በደረሰው አደጋ ቢያንስ 300 የሚሆኑ ሰዎች የተረፉ ሲሆን እስከ 200 የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ እስካሁን የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት ከዋና ከተማዋ ኪንሻሳ በስተምስራቅ በኩል በሚገኘው ወንዝ ላይ ትጓዝ የነበረችው ጀልባ ከትልቅ አለት ጋር ተጋጭታለች።
አደጋው ሲደርስ ጀልባዋ ስትጓዝ የነበረው በምሽት ሲሆን በአገሪቱ ህግ መሰረት በምሽት ወንዝ ላይ መጓዝ ክልክል ነው።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመንገድ ዘርፉ ደካማ በመሆኑ ምክንያት በርካታ ዜጎች ረጅም ርቀት ጉዞ ሲያደርጉ ጀልባዎችን ይመርጣሉ።
የአገሪቱ የሰብአዊ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ስቲቭ ምቢካዬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጀልባዋ ከመገልበጧ በፊት በርካታ ሰዎችን ጭና በምሽት ስትጓዝ እንደነበር ከአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ ደርሷቸዋል።
'' 60 ሰዎችን ለቀጠፈው አደጋው መድረስ ምከንያቱ በምሽት መጓዛቸው ነው። ከአደጋው በኋላ ባደረግው አሰሳ 300 ሰዎችን ማዳን የቻልን ሲሆን አሁንም ቢሆን የፍለጋ ስራው ቀጥሏል'' ብለዋል
የአካባቢው መንግስት ቃል አቀባይ ቻርለስ ምቡታሙንቱ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ምሽት አንድ ሰአት ላይ ነው።
''ነዋሪዎች አደጋውን ተከትሎ አስክሬኖች በወንዙ ላይ ሲንሳፈፉ እንደነበር ነግረውናል'' ብለዋል ቃል አቀባዩ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ሲገልጹ።
በዴሞክራቲክ ኮንጎ ተመሳሳይ የጀልባ አደጋዎች የተለመዱ ሲሆን ብዙ ጊዜ ጀልባዎቹ መጫን ከሚገባቸውና ከሚችሉት በላይ ተሳፋሪዎችን ጭነው ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።
ሌላው ቢቀር ዋና የማይችሉ ሰዎች እንኳን እንዴት እራሳቸውን ከሞት ማዳን እንደሚችሉ የጥንቃቄ መረጃ አይሰጣቸውም።
ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ 'ኪቩ' ሀይቅ ላይ አንዲት ጀልባ ተገልብጣ 167 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።
ይህ አደጋ ተከትሎም ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺሰኬዲ በጀልባ ላይ የሚጓዙ ሰዎች የህይወት አድን ጃኬት ማድረግ ግዴታ እንዲሆን አድርገው ነበር።
ነገር ግን በዚህኛው ጀልባ ላይ ተሳፍረው የነበሩት ዜጎች መከላከያ ጃኬቱን ስለማድረጋቸው አልያም ስላለማድረጋቸው የታወቀ ነገር የለም ተብሏል።