ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ፡ “የካፒቶል ሒል ነውጥ”ን የሚመረምር ገለልተኛ ኮሚሽን ሊቋቋም ነው
በአሜሪካ የታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲ፣ "ኮንግረስ የካፒቶል ሒል ነውጥን የሚረምር ገለልተኛ ኮሚሽን ያቋቁማል" ሲሉ ተናገሩ።
ጥር 6፣ በተለምዶ "የካፒቶል ሒል ነውጥ" ተብሎ የሚጠራው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች የሁለቱ ምክር ቤቶች መሰብሰብያና በርካታ የመንግሥት አስተዳደር ቢሮዎችን ሰብረው በመግባት የዲሞክራሲ ተምሳሌት ተደርጎ የሚታየውን ስፍራ እንዲሁም የአገሪቱን ስምና ክብር የሚያጎድፍ ተግባር የፈጸሙበት ዕለት ነው።
አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲ ለሕግ አውጪው ምክር ቤት በጻፉት ጠንካራ ደብዳቤ "ገለልተኛ ኮሚሽኑ የመስከረም 11 በኒውዯርክ መንትያ ሕንጻዎችና በፔንታጎን የደረሰውን ጥቃት የሚመረምረው ኮሚሽን በተቋቋመበት መንገድ የሚቋቋም ይሆናል።
"ነውጡ እንዴት ሊከሰት እንደቻለ በጠራ መንገድ ማወቅ ይኖርብናል" ብለዋል ናንሲ።
በአሜሪካ ታሪክ ለ2ኛ ጊዜ በመከሰስ የመጀመርያ ሆነው የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ አመጽን ቀስቅሶ ከመምራት ክስ ነጻ መደረጋቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ነጻ ያደረጋቸው ሪፐብሊካን እንደራሴዎች ለክሱ በቂ ድጋፍ ሳይሰጡት በመቅረታቸው ነበር።
ሆኖም ዲሞክራቶችና አንዳንድ ሪፐብሊካኖች ጭምር ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን በመቋቋሙ ላይ ስምምነት አላቸው።
በጥር 6ቱ ነውጥ አምስት ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
የሚቋቋመው ገለልተኛ ኮሚሽን ነውጡን ማን አነሳው፣ እንዴት ተመራ፣ እነማን ተሳተፉበት፣ የትኛው የመንግሥት ባለሥልጣንና አካል እገዛ ሰጠ፣ ማስቆም ለምን አልተቻለም በሚሉና በሌሎች ጉዳዮች ዙርያ አጥጋቢ መልስ ይዞ እንዲመጣ ይፈለጋል።
በተለይም የካፒቶል ሒል ፖሊስ ነውጡን ለማስቆም የነበረው ዝግጁነትና ፍቃደኝነት ይመረምራል ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ ይህን ነውጥ በማነሳሳት ተከሰው የነበረ ቢሆንም ሴኔቱ ሁለት 3ኛ ድምጽ ሊሰጥ ባለመቻሉ ባለፈው ቅዳሜ ከክሱ ነጻ ተብለዋል።
በድምጽ ሂደቱ 7 ሪፐብሊካኖችና 2 ገለልተኛ እንደራሴዎች ወደ ዲሞክራቶች በመወገን ይከሰሱ በሚል ድምጽ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም ትራምፕን ለመክሰስ የሚሆነው የ2 ሦስተኛ የበላይነት ግን ሊገኝ አልቻለም።