ሪፐብሊካኖች የትራምፕ 'የፍርድ ሂደት ፍትሃዊ ለማድረግ' እንዲዘገይ ጠየቁ

የአሜሪካ ሪፐብሊካን የህግ መምሪያ ምክር ቤት እንደራሴዎች የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ክስ እስከሚቀጥለው ወር እንዲራዘም ዲሞክራቶችን ጠይቀዋል።

ሪፐብሊካኖቹ ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለፍርዱ ሂደት ዝግጅት ጊዜ እንዲያገኙ ነው። የቀድሞው ፕሬዚዳንት በቅርቡ የተከሰተውን የካፒቶሉን ነውጥ አነሳስተዋል በሚል እንዲከሰሱ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

ከስልጣን ሊለቁ ጥቂት ቀናት በቀራቸው ወቅት ያለመከሰስ መብታቸው እንዲገፈፍና በአመፅና ሁከት እንዲከሰሱም ለማስቻል እንደራሴዎቹ በአብላጫ ድምፅ መወሰናቸው የሚታወስ ነው።

ለሪፐብሊካን አቻቸው ጥሪ ያደረጉት ሚክ ማኮኔል ዲሞክራት እንደራሴዎች የመጀመሪያ ሂደት ክሱን ከማቅረብ እንዲዘገዩና ትራምፕም ለዝግጅት ሁለት ሳምንት ያህል እንዲኖራቸው ጠይቀዋል።

የክሱ ሂደት በአውሮፓውያኑ የካቲት አጋማሽ ላይ ቢጀመር ለትራምፕ በቂ ጊዜ ይኖራቸዋል ብለዋል።

ከትናንት ጀምሮ ሪፐብሊካኖች በምክር ቤቱ አብላጫ ወንበር መኖሩን ማቆም ተከትሎ የዲሞክራቶች መሪ ቹክ ሹመር በሃሳቡ ላይ ይስማማ ዘንድ ግድ ይላል ተብሏል።

የዲሞክራት እንደራሴዎች በበኩላቸው ክሱን ለምክር ቤቱ ለማቅረብ ዝግጅታቸውን ጨርሷል ተብሏል።

በትናንትናው ዕለት ይፋዊ የስልጣን ዘመናቸው ያበቃው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተከታያቸውን ጆ ባይደንን በዓለ ሲመት ሳይታደሙ ወደ ፍሎሪዳ አቅንተዋል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከወር በፊት ነበር በዋይት ሃውስ አቅራቢያ ለነበሩ ሰልፈኞች "በሰላማዊና በአርበኝነት" ድምፃቸው እንዲሰማ እንዲያደርጉ ጥሪ ያስተላለፉት።

ነውጠኛ ሰልፈኞቹ ወደ አሜሪካው ካፒቶል ህንፃ እየተቃረቡ ነበር ተብሏል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት አክለውም "በእልህ እንዲታገሉም" ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።

ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸውም ወደ ካፒቶል ሂል ህንፃ ሰብረው ገቡ፤ ከፍተኛ ሁከት ተነሳ።

በወቅቱም በህንፃው የምክር ቤቱ እንደራሴዎች ተመራጭ የነበሩትን የጆ ባይደንን ፕሬዚዳንታዊ ድል ይፋዊ ለማድረግ ስብሰባ ላይ ነበሩ።

በተነሳውም ሁከት አራት ተቃዋሚዎች ሲገደሉ በቦታው የነበረ የካፒቶል ፖሊስም ተገድሏል።

ሁከቱና ነውጡ ከተነሳ ከሳምንት በኋላ በስልጣን ላይ እያሉ ሁለት ጊዜ እንዲከሰሱ የተወሰነባቸው ወይም ኮንግረሱ በወንጀሎች የጠየቃቸው የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆኑ።

ከስልጣን ከተገለሉ በኋላ የፍርድ ሂደታቸው በምክር ቤቱ የሚታይ የመጀመሪያ ሰው አድርጓቸዋል።

ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙም እስከ ወዲያኛው ድረስ መቼም ቢሆን በስልጣን ቦታ ላይ እንዳይቀመጡ ይደረጋል።