ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአየር ብክለት፡ ስድስት ሚሊየን እንግሊዛውያን ከባድ የሳምባ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል ተባለ
እድሜያቸው ከ65 በላይ የሆኑ ወደ ስድስት ሚሊየን የሚጠጉ እንግሊዛውያን ከባድ ለሆነ ሳምባ ጉዳትና አስም ሊጋለጡ እንደሚችሉ አንድ አዲስ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። ምክንያቱ ደግሞ የተበከለ አየር ነው ተብሏል።
በጥናቱ መሰረት እድሜያቸው የገፉ ሰዎችና ከዚህ ቀደም የመተንፈሻ አካላት በተለይ የሳምባ ችግር ያለባቸው ሰዎች በአየር ብክለት ጉዳት የሚደርስባቸው ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ ከሌሎች በተለየ ተጋላጭም ናቸው ተብሏል።
ጥናቱን የሰሩት የእንግሊዝ ሳምባ ፋውንዴሽን እና 'አዝመ ዩኬ' ናቸው ተብሏል።
በርካታ የህዝብ እንደራሴዎች መንግስት የአየር ብክለትን በተመለከተ ጠበቅ ያሉ እርምጃዎችን እንዲወስድ እየወተወቱ ይገኛሉ።
''በዩኬ ከወረርሽኙ በኋላ በሚደረጉ የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ውስጥ የምንተነፍሰውን አየር ጥራት ማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል'' ብለዋል በአየር ንብረት ላይ የሚያተኩረው ኮሚቴ አባል የሆኑ አንድ የሕዝብ ተወካይ።
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ሁለቱ ተቋማት የሰሩት ጥናት እንደሚለው ከሆነ በተበከለአየር ውስጥ የሚገኙት ንጥረ ነገሮች ወደ ሳምባችን ከገቡ በኋላ ወደ ደም ስራችንም ይሰራጫሉ።
ይህ ደግሞ ከሳምባ በተጨማሪ የደም ቧምቧዎቻችንም ሊጎዱ እንደሚችሉ ማሳያ ነው ተብሏል።
እነዚህ ጎጂ ንጥረ ነገሮች ሁሉንም ሰው የሚያጠቁ ሲሆን ጉዳታቸው ግን እድሜያቸው የገፋ ሰዎች ላይ ይረታል። ሳምባቸውን በማዳከም ወደ ከፍተኛ የመተንፈስ ችግር ውስጥ እከታቸዋል።
የአየር ብክለት በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በጣም የተንሰራፋ ነገር ነው ይላሉ በጥናቱ ላይ የተሳተፉት ዶክተር ኒክ ሆፕኪንስ።
ዶክተሩ እንደሚሉት በየዓመቱ ከ30 ሺ እስከ 40 ሺ የሚደርሱ መከላከል የሚቻሉ ሞቶች ምክንያታቸው ለተበከለ አየር መጋለጥ ሊሆን እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ።
የአየር ብክለት ከዚህ በተጨማሪም የአንድን ሰው በሳምባ ካንሰር የመያዝ እድል ከፍ የሚያደርግ ሲሆን ለተለያዩ የልብ ህመሞችም ቢሆን የማጋጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነው።
''ሁላችንም እንደምነዋቀው እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ለተበለከ አየር የመጋለጥ እድላቸው የሰፋ ነው፤ ደሀው የማህበረሰብ ክፍል የሚኖርባቸው አካባቢዎች ደግሞ ያላቸው የንጹህ አየር መጠን ዝቅተኛ ነው። ስለዚህ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው አረጋውያን በቀላሉ በአየር ብክለት ይጎዳሉ'' ይላሉ ዶክተር ኒክ ሆፕኪንስ።
ጥናቱን ያካሄዱት ሁለቱ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ተቋማት መንግስት ዜጎች የሚተነፍሱትን አየር ጥራት የሚቆጣጠር ሚኒስትር መስሪያ ቤት እንዲያቋቁምና ብሄራዊ የጤና ስርአቱን ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ እንዲሰራ ጥሪያቸው አቅርበዋል።
ኪምበርሊ ኮል ከባድ የሳምባ ችግር ያለባት ሲሆን የተበከ አየር ስትተንፍስ ደግሞ ህመሟ እንደሚጠናባት ትናገራለች። ሳምባዋ በጣም ጉዳት ስለደረሰበት ልክ የተበከለ አየር ስትተነፍስ ወዲያው ህመሙ ይጀምራታል። በቀላሉ ንጹህና የተበከለ አየር መለየት እንደምትችልም ትገልጻለች።
''አንዳንድ ጊዜ በእጅጉ የተበከለ አየር ስተንፍስ ሳምባዬ ይደማል። አንዳንድ ጊዜ በጣም ያስለኝና ለቀናት እታመማለው።''
የተሰራውን ጥናት ተከትሎ የአካበቢ ጥበቃ ሚኒስትሯ ሬቤካ ፖው ''ከ2010 በኋላ የአየር ብክለት በእጅጉ ቀንሷል፤ የበካይ ንጥረነገሮች ልቀትም ቢሆን 9 በመቶ መቀነስ ተችሏል። ነገር ግን አሁንም ብዙ መሰራት ያለባቸው በገሮች እንዳሉ እናምናለን'' ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።