በሚየንማር ተቃውሞ መበርታቱን ተከትሎ ኢንተርኔት ማቋረጡ ተገለፀ

ሚያናማር ተቃዋሚዎች
የምስሉ መግለጫ, ሚያናማር ተቃዋሚዎች

የሚየንማር ጦር መሪዎች የአገሪቱን ኢንተርኔት መዝጋታቸውን የዓለም አቀፍ ኢንተርኔትን ፍሰት የሚከታተለው ቡድን አስታወቀ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚየንማር ወታደር ያካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት በመቃወም ሠልፍ እያካሄዱ ነው።

ኔት ብሎክስ የተሰኘው የኢንተርኔትን ፍሰት የሚከታተለው ተቋም የአገሪቱ የኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ ሊባል ደረጃ መቋረጡን አስታውቋል።

የቢቢሲ በርማ ቋንቋ አገልግሎትም የኢንተርኔት መቋረጡን አረጋግጧል።

ወታደራዊ ኃይሉ ሰኞ ዕለት መፈንቅለ መንግሥት ካካሄደ ወዲህ ትልቁ ነው የተባለ የተቃውሞ ሠልፍ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።

"ወታደራዊ አምባገነንነትይውደም፤ ዲሞክራሲ ይለምልም" የሚል መፈክሮች የያዙ ሰልፈኞች በዋና ከተማዋ ያንጎን ጎዳናዎች ታይተዋል።

የመከላከያ ቆብ ያደረጉና ጋሻ የያዙ ፖሊሶች ሰልፈኞቹን ወደ ማዕከላዊው የከተማ ክፍል እንዳይሄዱ አግደዋቸዋል።

በሚየንማር በማሕበራዊ መገናኛ ብዙኀን ተቃውሞ ሰልፎች ጥሪ እንዳይደረግ በሚል ፌስቡክ ከተቋረጠ ከአንድ ቀን በኋላ ትዊተር እና ኢንስታግራምም ታግዷል።

ወታደራዊ ኃይሉ በማህበራዊ ሚዲያዎቹ መታገድ ላይ አስተያየታቸውን አልሰጡም።

ትዊተር እና ኢንስታግራምን በሚየንማር

ቴሌኖር የተባለው የአገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ተጠቃሚዎቹ ትዊተር እና ኢንስታግራምን እንዳይጠቀሙ እንዲያግድ መደረጉን ይፋ አድርጓል። ጦሩ ፌስቡክን ባሳለፍነው ሐሙስ ማገዱ ይታወሳል።

በቀድሞዋ በርማ በአሁኗ ሚየንማር በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የአገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ ሥልጣን መቆጣጠሩ ይታወሳል።

ወታደሮቹ የሥልጣን መንበሩን መያዛቸውን ይፋ ያደረጉት የኖቤል ሰላም ሽልማት ተሸላሚዋ ኦንግ ሳን ሱ ቺ እና ሌሎች የፖለቲካ መሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ተከትሎ ነበር።

በአገሪቱ የተደረገውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ በጦሩ ላይ ተቃውሞ እየበረታ ይገኛል።

በያንጎን ከተማ ተማሪዎች እና መምህራን አደባባይ በመውጣት ኦንግ ሳን ሱ ቺ እና ለሲቪል መሪዎቻቸው ያላቸውን ድጋፍ አሰምተዋል።

እንደ ሳን ሱ ቺ ጠበቃ ከሆነ የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት በቁም እስር ላይ የሚገኙ ሲሆን ፖሊስ በሕገ-ወጥ መንገድ የግንኙነት መሳሪያዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በመኖሪያ ቤታቸው ተጠቅመዋል የሚል ክስ መስርቶባቸዋል።

ሐበራዊ ሚዲያዎች ለምን ተዘጉ?

በሚየንማር ኢንተርኔት ፌስቡክ ነው ይባላል። የአገሪቱ ዜጎቹ ጦሩ መፈንቅለ መንግሥት ሲያደርግ በቀጥታ በፌስቡክ ተመልክተውታል።

በርካታ ሲቪል መሪዎች በአገሪቱ ጦር አባላት ከመኖሪያ ቤታቸው ሲለቀሙ በፌስቡክ በቀጥታ ተሰራጭቷል። መፈንቅለ መንግሥቱን የሚቀወሙ የተለያየ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች በፌስቡክ፣ ትዊተር እና ኢንስታግራም ተሰራጭቷል።

በዚህም ጦሩ የሚነሳበትን ተቃውሞ ለማብረድ እና የመረጃ ስርጭትን ለመግታት ማህበራዊ ሚዲያውን ለመዝጋት መገደዱን የቀጠናው ተንታኞች ይናገራሉ።

የትዊተር ቃል አባይ “ሰዎች ድምጻቸውን የማሰማት መብታቸው ተገፏል” ያሉ ሲሆን፤ የኢንስታግራም ባለቤት የሆነው ፌስቡክ ደግሞ፤ ለሚየንማር ባለስልጣናት “ግንኙነቱን ማስጀመር አለባቸው። ሰዎች ከቤተሰብ እና ጓደኞቻቸው ጋር እንዲገናኙ እና መረጃ እንዲኖራቸው መፍቀድ አለባቸው” ሲል መልዕክት አስተላልፏል።

ለጦሩ መፈንቅለ መንግሥት የዜጎች ምላሽ

ጦሩ ስልጣን በኃይል መቆጣጠሩን የሚቃወሙ በርካቶች ሲሆኑ በተለይም መምህራንና ተማሪዎች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው ተብሏል።

በንግድ ከተማዋ ያንጎን በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ተቃዋሚዎች በኃይል የተገረሰሱትንና በእስር ላይ የሚገኙትን መሪ ኦንግ ሳን ሱ ቺ ስም እያነሱ መፈክር ሲያሰሙ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የፓርቲያቸውን ቀለም የሚወክል ቀይ ሪባን አድርገው ታይተዋል።

መፈንቅለ መንግሥት ከተከሰተበት ከሰኞ እለት ጀምሮ ለህዝብ ያልታዩት ኦንግ ሳን ሱ ቺ በቤት ውስጥ እስር እንደሚገኙ አንድ የፓርቲያቸው ባለስልጣን አስታውቋል።

የቀድሞዋ በርማ በመፈንቅለ መንግሥቱ ማግስት ፀጥታ ወሯት የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን አመፆች ተቀጣጥለዋል ተብሏል።

"የኛ ትውልድ በእንደዚህ አይነት አምባገነን ስርአት እንዲሰቃይ አንፈቅድም" በማለት ሚን ስትሁ የተሰኘች ተማሪ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግራለች።