የሚያንማር መፈንቅለ መንግሥት፡ አሁን ለምን? በቀጣይስ?

ኦንግ ሳን ሱ ቺ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በቀድሞዋ በርማ በአሁኗ ሚያንማር ወታደሩ ሥልጣን መቆጣጠሩ ተሰምቷል።

ወታደሮች ሥልጣን መቆጣጠራቸውን ይፋ ያደረጉት የሲቪል መንግሥት አባላትን በቁጥጥር ሥር ማድረጋቸውንተከትሎ ነው።

የኖቤል ሰላም ሽልማት ተሸላሚዋ ኦንግ ሳን ሱ ቺ እና ሌሎች የፖለቲካ መሪዎች ተለቅመው ወዳልታወቀ ሥፍራ ተወስደዋል።

ይህ መፈንቅለ መንግሥት በአገሪቷ ዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ፍርሃትን ፈጥሯል። በርማ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንደምትሸጋገር ተስፋን ሰንቀው ለነበሩት ዜጎች የሳን ሱ ቺ እና ሌሎች ሲቪል ፖለቲከኞች እስር የዲሞክራሲ ተስፋን ያጨለመ ሆኗል።

ላለፉት አምስት ዓመታት በአንድ ወቅት ታግዶ የነበረው የብሔራዊ ዲሞክራሲ ሊግ (ናሽናል ሊግ ፎርዲሞክራሲ) ከ25 ዓመታት በኋላ የተካሄደውን ምርጫ በማሸነፍ እአአ 2105 ላይ መንበረ ስልጣኑን ተረክቦ ነበር።

ፓርቲው ሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመኑን መጀመር ሲገባው ነበር ዛሬ ንጋት ላይ መፈንቅለ መንግሥት የተፈጸመው።

በሚያንማር በወታደሩ እና በሲቪል አስተዳደሩ መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውጥረት ተከስቶ ነበር።

እነ ሳን ሱ ቺ ከመታሰራቸው በፊት የመንግሥት ቴሌቪዥን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ነበር።

ሚያንማር የዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ እስከጀመረችበት 2011 ድረስ በጥብቅ ወታደራዊ መንግሥት ነበር ስትመራ የቆየችው።

ባለፈው ሕዳር በተደረገ ምርጫ የሳን ሱ ቺ ፓርቲ 'ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ' መንግሥት ለመመሥረት ሚያስችለውን የመቀመጫ ቁጥር ማግኘት ችሎ ነበር። ሆኖም ወታደሮቹ ምርጫው ተጭበርብሯል ሲሉ ቆይተዋል።

ከሁለት ወራት በፊት ተካሂዶ በነበረው ምርጫ የሳን ሱ ቺ ፓርቲ ባለፈው ህዳር በተደረገ ምርጫ 83% መቀመጫ አሸንፎ ነበር። ይህም ለሳን ሱ ቺ መንግሥት ሕዝብ ይሁንታን መስጠቱን የሚያሳይ ተደርጎ ነበር የተወሰደው።

የአገሪቱ ጦር ግን ምርጫው ተጭበርብሯል ሲል ቆይቷል። የሂዩማን ራይትስ ዎች የእስያ ምክትል ዳይሬክተር ፊል ሮበርትሰን ግን ጦሩ ምርጫው ተጭበርብሯል ሲል የቆየው ምርጫው ለመጭበርበሩ የሚያረጋግጥም አንድም ማስረጃ ሳያቀርብ ነው ይላል።

ጦሩ ይህን መሰል ወቀሳዎቸን ሲያቀርብ የነበረው መፈንቅለ መንግሥት ለማከናወን ሁኔታዎችን ሲያመቻች ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

ፊል ሮበርትስ ጦሩ አገሪቷን በመቆጣጠሩ በርማ ከተቀረው ዓለም ነጥሎ ሊገዛ እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ

የሚያንማር ጦር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የሚያንማር ጦር

ዛሬ የሆነው ምን ነበር?

ዛሬ [ሰኞ] ወታደሮች የአገሪቱን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውና መሪያቸውም ኮማንደር ሚነ ኦንግ ሌይንግ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በርካታ ወታደሮች በአገሪቱ ዋና ከተማ ናይፒታው እና በሌላኛዋ ትልቋ ከተማ ያንጎን ይታያሉ።

የሞባይልና ኢንተርኔ አገልግሎት እንዲሁም ስልክ በስፋት የተቋረጠባቸው ዋና ዋና ከተሞች ላይ ሲሆን የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ሥርጭት ለማድረስ እክል ገጥሞኛል በማለት ተቋርጧል።

በርካታ ወታደሮችም በተለያዩ ቦታዎች እየሄዱ የሲቪል አስተዳደሩ ሚኒስትሮች የነበሩ ሰዎችን በቁጥጥር ሥርእንዳዋሉ ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።

የቢቢሲዋ የደቡብ ምሥራቅ ኢሲያ ወኪል እንደምትለው ከሆነ ሳን ሱ ቺ በአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት አላቸው። ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ያላትን ሳን ሱ ቺን የመሰሉ ፖለቲከኞችን ማሰር ትልቅ ውሳኔ ነው።

ይህ ምርጫ የወታደራዊ መንግሥት አስተዳደር ካበቃበት ከ2011 ወዲህ ሲካሄድ ለ2ኛ ጊዜ ነው።

ነገር ግን ይህን ምርጫ ወታደሩ ሳይቀበለው ቀርቶ ነበር።

ይህን ተከትሎም ምናልባት ወታደሩ መፈንቅለ መንግሥት ያደርግ ይሆናል የሚል ፍርሃት ነግሶ ቆይቶ ነበር።

ኦንግ ሳን ሱ ቺ ማን ናቸው?

ሳን ሱ ቺ የበርማ የነጻነት አባት የሚባሉት የጄኔራል ኦንግ ሳን ሴት ልጅ ናት።

አባቷ የተገደሉት እሷ ገና የ2 ዓመት ልጅ ሳለች ነበር። የተገደሉትም በርማ ከእንግሊዝ ነጻነቷን ከመቀዳጀቷ ጥቂት ቀደም ብሎ በፈረንጆቹ በ1948 ነበር።

ሳን ሱ ቺ በአንድ ወቅት ለዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ትልቅ ተምሳሌት ተደርጋ ነበር የምትታየው። ምክንያቱም ምሕረት አያውቁም ከሚባሉት የምያንማር ወታደራዊ ኃይሎች በተጻጻራሪ በመቆም በአገሪቱ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን በመታገል ረዥም ዓመታት አሳልፋለች።

ይህን ተከትሎም በ1991 የኖቤል የሰላም ሽልማትን ማሸነፍ ችላ ነበር።

ሽልማቱን ያሸነፈችውም በቁም እስር ላይ ሳለች ነበር።

ሳን ሱ ቺ ለ15 ዓመታት በእስር ከቆየች በኋላ በ2010 ነጻ ተደርጋለች።

በ25 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገ ምርጫም ፓርቲዋ ትልቅ ድል አግኝቶ ወደ ሥልጣን መምጣት ችሎ ነበር።

ሆኖም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሳን ሱ ቺ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት እንድትሆን አይፈቅድም። ምክንያቱም ልጆቿ የውጭ ዜጎች ስለሆኑ ነው። በዚህም የተነሳ መንግሥትን የምትመራው ከጀርባ ሆና ነው።

ሳን ሱ ቺ አሁን 75 ዓመት ሆኗታል።

የሰላም ኖቤል አሸናፊ የነበረችው ሳን ሱ ቺ በአገሯ የሮሒንጋ ሙስሊሞች ላይ ለደረሰው ግፍና መከራ ቸልተኝነት በማሳየቷ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያገኘቻቸው ክብርና እውቅናዎችን ተነጥቃለች።

ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ሔግ ቀርባ ለዚህ ምላሽ እንድትሰጥ በተደረገበት ጊዜ በሮሒንጋ ሙስሊሞችላይ የደረሰውን ግፍ ተገቢነቱን ለማሳየት መሞከሯ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰጥቷት የነበረውን ክብር የሚያጠለሽ ሆኖ ተገኝቷል።

ሆኖም በአገሯ ውስጥ ሳን ሱ ቺ በቡድሃ ብዙኃን ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት አላት።