ትግራይ፡ የዓይነ ሥውሩ ፖለቲከኛ ሞት ስለ ኢትዮጵያው ግጭት ምን ይነግረናል?

በስቃይ እና መከራ የተሞላው የአስመላሽ ወልደ ሥላሴ ሕይወት እና አሁን ደሞ ሕልፈታቸው በኢትዮጵያው በሰሜን ትግራይ ተራሮች እየተካሄደ ያለው ግጭት ምን ያህል አስቀያሚ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡
ሕወሓት ትጥቅ ትግል በጀመረበት እኤአ እንደ 1975 ዓ.ም ግድም ትግሉን የተቀላቀሉት ታጋይ አስመላሽ፣ የዐይን ብርሃናቸውን ያጡት በቦምብ ፍንዳታ በደረሰባቸው ጉዳት ነበር፡፡ በቦንብ ፍንጣሪ የተመቱት አምባላጌ ተራሮች ምሽግ ውስጥ ነበር፡፡ ያ የትጥቅ ትግል እንደ አውሮጳዊያኑ በ1991 ዓ.ም ዋና ከተማዋን አዲስ አበባ በመቆጣጠር እና ወታደራዊውን ሥርዓት በማስወገድ ተጠናቋል፡፡
ከዚያ በ1998 (እኤአ) ሕወሃት-መራሹ ኃይል ከኤርትራ ጋር ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት ሲያደርግ፣ አቶ አስመላሽ የግራ እጃቸውን አጡ፡፡ ያን ጊዜ በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ነበሩ፡፡ የግራ እጃቸውን ያሳጣቸው የኤርትራ የአየር ድብደባ ነበር፡፡
ሕወሃትን ወደ ሽምቅ ተዋጊነት በመለሰው ያሁኑ ጦርነት ደግሞ፣ ታጋይ አስመላሽ ተገደሉ፡፡ የሕወሃት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና ከፍተኛ አመራር የነበሩት አስመላሽ የተገደሉት ከቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሥዩም መስፍን እና ከቀድሞው የፌዴራል ጉዳዮች ሚንስትር አባይ ጸሐዬ ጋር ነው፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እነዚህ አመራሮች የተገደሉበትን ወታደራዊ ኦፕሬሽን ያዘዙት የ44 ዐመቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ወደ ከፍተኛው የሥልጣን እርከን እስኪመጡ ድረስ በኢሕአዴግ-መራሹ መንግሥት ውስጥ እምብዛም የማይታወቁ አባል ነበሩ፡፡
አሁን እሳቸው እና ሕወሓት ጠላቶች ሆነዋል፡፡ ወደ ቀይ ባሕር መውጫ የሆነችውን ኤርትራንና ሱዳንን በመዋሰን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለውን ትግራይ ክልልን ለመቆጣጠርም እየተፋለሙ ነው የሚገኙት፡፡
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያን ሠራዊት ለማገዝ ወታደሮቻቸውን እንደላኩ ይነገራል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ኢሳያስ ወታደሮቻቸውን የላኩት እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር ከ1998 እስከ 2000 ዓ.ም በተደረገው የድንበር ጦርነት በሕወሃት ክንድ የደረሰባቸውን ውርደት ለመበቀል ነው፡፡ በዚያ ደም አፋሳሽ ጦርነት ያለቁት ሰዎች ብዛት እስከ 100 ሺህ ይደርሳል፡፡
ሁለቱም መንግሥታት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ መገኘታቸውን ያስተባብላሉ፡፡ ሆኖም ብዙ የትግራይ ዐይን እማኞች፣ ኤርትራዊያን እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ምድር እንዳሉ ነው የሚናገሩት፡፡
ዐቢይ አሕመድ በህወሓት ላይ ድል መቀዳጀታቸውን ያወጁት የትግራይ ዋና ከተማ መቀሌ በተያዘች ማግስት ነበር፡፡ ያንን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትሩ 250 ሺህ ተዋጊዎች እንደነበሩት የሚነገርለትን የሕወሃት አመራሮች አድኖ የመያዝ ዘመቻ እንደሚቀጥል ቃል ገቡ፡፡
እጅን ታስሮ እና ተጎሳቁሎ መታየት
ሁሉም ከ60ዎቹ ዕድሜ በላይ ናቸው፤ አስመላሽ፣ ሥዩም እና አባይ፡፡ በምን አኳኋን እንደተገደሉ ግን በግልጽ አይታወቅም፡፡ አንዳንዶች ተይዘው እንደተረሸኑ ይገምታሉ፡፡ በመንግሥት በኩል የሚነገረው ግን በአንድ ዋሻ አቅራቢያ እጅ ስጡ ሲባሉ አሻፈረኝ በማለታቸው የተወሰደ ርምጃ እንደሆነ ነው፡፡
የእነዚህ ሦስት ታጋዮች መገደል የተሰማው የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ ነው፡፡ አቶ ስብሐት ነጋ አንዱ ናቸው፡፡ ስብሃት በካሜራ ፊት እጃቸው ታስሮ እና ተጎሳቁለው የታዩበት ሁኔታ፣ እኤአ በ2003 ሳዳም ሁሴን የተያዙበትን የሚያስታውስ ነው፡፡
አቶ ፈይሳል ሮቤል መቀመጫውን አሜሪካ ካደረገው የሆርን ኦፍ አፍሪካ ስተዲስ ባልደረባ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት የዐቢይ ደጋፊዎች ሀገሪቱን ለ3 ዐሥርት ዐመታት ያህል በጠንካራ ክንዱ የመራው የሕወሃት ባለሥልጣናት በገጠማቸው ዕጣ ፋንታ ደስተኞች ናቸው፡፡ ህወሓት መሪነቱን ያጣው በአገሪቱ ተቃዋሚዎች ሰልፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ በመጣ ለውጥ ነው፡፡ ለውጡ ዐቢይን ለሥልጣን አብቅቷቸዋል፡፡
"ህወሃትን አገኘነው፡፡ ከመድረ ገጽ እያጠፋነው ነው፡፡ ከእንግዲህ ተነስተው ሊጨቁኑን አይችሉም" የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ህወሓትን የማይወዱት ትግራዋያን ጭምር እያሉ ያሉት ሌላ ነው፡፡ "ዓይነ ስውሩን አስመላሽን ገደላችሁ፡፡ የወገብ ቀዶ ጥገና አድርጎ ለመራመድ እንኳ የሚቸገረውን ሥዩምን ገደላችሁ፡፡ የልብ ቀዶ ጥገና ያደረገውን አባይን ገደላችሁ፡፡ ሁለት ፎቅ እንኳ ችለው የማይወጡትን አቦይ ስብሐትን አዋረዳችሁ፡፡ እነዚህ እኮ ለእኛ ጀግኖቻችን ናቸው" ነው የሚሉት፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በስደት ላይ የሚገኙትና በሰብዓዊ መብቶች ዙርያ ዘመቻ በማድረግ የሚታወቁት አቶ ጳውሎስ ተስፋ ጊዮርጊስ እንደሚሉት፣ ጦርነቱ በተጀመረ በሦስተኛው ወር ግድም የህወሓት ሰራዊት በተፈጸመበት የድሮን ጥቃት ከባድ ኪሳራ እንደደረሰበት አጠያያቂ አልነበረም፡፡ ከድሮን በተጨማሪ በርካታ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወታደሮች ብሎም ከትግራይ ክልል ጋር በመሬት ይገባኛል ጥያቄ የሚወዛገበው አማራ ክልል ታጣቂዎች በጥቃቱ መሳተፋቸው ከባድ ጉዳት አድርሷል፡፡
‹‹ህወሓት ሰፊ መሬቶችን፣ በርካታ ተዋጊዎችን፣ በርካታ መሪዎችን፣ በርካታ ከባድ መሣሪያዎችን በጦርነቱ አጥቷል፡፡ አሁን በእጁ ያሉት መካከለኛና ቀላል መሣሪያዎች ብቻ ናቸው፡፡ ኤርትራ በዚህ ደረጃ በዚህ ጦርነት ውስጥ ትገባለች ብሎ ሕወሃት በፍጹም የጠበቀ አይመስለኝም፡፡››
"ኢሳያስ የድሮ የጦርነት ዘዴያቸውን ነው የተጠቀሙት፡፡ ጠላትን በብዙ ታንክ፣ በብዙ ወታደሮች፣ በብዙ መሣሪያዎች እና በብዙ ቦምብ በአንድ ጊዜ የመጨፍለቅ ስትራቴጂ፡፡" አቶ ጳውሎስ በመቀጠልም፣ ‹‹ነገር ግን ህወሃት አሁንም አላበቃለትም፡፡ ከባድ ውጊያዎችን አድርጓል፡፡ አሁን ሽምቅ ውጊያ ለማድረግ፣ በደንብ ወደሚያውቀው ገጠራማዋ ትግራይ ማለትም ወደ ተራሮች እና ኮረብታዎች ተመልሷል፡፡››
የጎንደር ዩኒቨርስቲ አስተማሪው ምንይችል መሠረት ግን ሕወሃት ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር መጠነ ሰፊ ጦርነት ካደረገ በኋላ ወደ ደፈጣ ውጊያ መግባቱ የራሱ የሆነ አደጋ አለው ባይ ናቸው፡፡ ‹‹በደፈጣ ተዋጊ ድርጅት ውስጥ አንድ አጥፍቶ ጠፊ ብዙ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ያው ሕወሃት የተረፉ ጥቂት ተዋጊዎች አሉት፡፡ በትግራይ አንዳንድ ተራራማ አካባቢዎችም ውጊያ እንዳለ ይሰማል፡፡ ሕወሃትም በአውራ ጎዳናዎች ላይ ደፈጣ ጥቃት ይፈጽማል፤ በዕርዳታ ካሚዮን ላይ ጭምር፡፡››

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ያንዣበበው የርሃብ ስጋት
እንደ አቶ ጳውሎስ ዕምነት ከሆነ፣ "መንግሥት ርሃብን እንደ መሳሪያ እየተጠቀመበት ነው፡፡ የመንግሥት ወታደሮች የአርሶ አደሩን ሰብል አቃጥለዋል፤ ጦርነቱ የተቀሰቀሰው በሰብል መሰብሰቢያ ወቅት ነው፡፡ ወታደሮች ከብቶችንም አርደዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው መንግሥት ትግራይን ሙሉ በሙሉ ዘግቶ በያዘበት ሁኔታ ነው፡፡ ምግብ እየገባ አልነበረም፡፡ አሁንም የምግብ ዕርዳታ ስርጭቱ የተገደበ ነው፡፡
"ሰዎች በምግብ ዕጥረት እየሞቱ ነው፡፡ ርሃብ ይከሰታል የሚል ስጋት አለ፡፡ ይሄ ጦርነት ርህራሄ የሌለበት ጦርነት ነው፡፡ እንዲያውም መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ባንድ ወቅት 'አሳውን ለማጥፋት፣ ባሕሩን አድርቅ' በማለት የተናገሩትን ያስታውሰኛል፡፡ የዐቢይ መንግሥት ሕወሃትን ለማዳከም፣ በርሃብ መቅጣትን ጨምሮ ሰላማዊውን የትግራይን ሕዝብ ማንበርከክ እንዳለበት አምኗል" ይላሉ አቶ ጳውሎስ።
የረድዔት ድርጅቶች እንደሚሉት፣ ጦርነቱ በኮሮና ወረርሽኝና በአንበጣ ወረራ ወቅት በመቀስቀሱ ችግሩን የከፋ አድርጎታል፡፡
- ባሁኑ ሰዓት ከ2 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ዕርዳታ ፈላጊ ሆኗል፡፡
- መጠነ ሰፊው መፈናቀል መጠነ ሰፊ የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭት እንዳያስከትል ስጋት አለ፡፡
- አሁን ከ40 ሆስፒታሎች ለሕዝቡ ተደራሽ የሆኑት 5 ብቻ ናቸው፡፡
- በሞተር የሚሰሩ የመጠጥ ውሃ ምንጮች አገልግሎት አቁመዋል፡፡
- ገበያዎች ከሞላ ጎደል ተሰናክለዋል፡፡
ቀውሱ በትግራይ ታሪክ ታይቶ እንደማይታወቅ በቅርቡ አንድ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሹም መናገራቸው በመገናኛ ብዙኀን ተዘግቧል፡፡ በባለሥልጣኑ ግምት፣ የክልሉ 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ይፈልጋል፡፡ ይሄ ደግሞ የክልሉ አጠቃላይ ሕዝብ 75 መቶኛው ማለት ነው፡፡ ከቀዬው የተፈናቀለው ሕዝብ ደግሞ 2.5 ሚሊዮን እንደሆነ እና ሦስት ሕጻናትን ጨምሮ 13 ሰዎች በርሃብ ስለመሞታቸው ቢሯቸው ሪፖርት እንደደረሰው ባለሥልጣኑ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት በበኩሉ ርሃብን እንደ መሳሪያ ተጠቅሟል የሚለውን ውንጀላ ያስተባብላል፡፡ አቶ ምንይችልም እንዲህ ያሉት ውንጀላዎች "ሙሉ በሙሉ ስህተት ናቸው" ባይ ናቸው፡፡ "መንግሥት በቂ የምግብ ዕርዳታ ክምችት አለው፡፡ ሆኖም ርዳታውን በገጠራማው ክፍል እንዳያሰራጭ የሕወሃት ሃይሎች ሹፌሮችን ይገድላሉ፡፡ የዐለማቀፉን ኅብረተሰብ አስተያየት ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር እና ሐዘኔታ ለማግኘት በማሰብ፣ መንግሥት ርሃብን እንደ መሳሪያ እየተጠቀመ እንደሆነ ለማስመሰል ጥረት እያደረገ ያለው ሕወሃት ነው፡፡
"ሕወሃት ለአርሶ አደሮች ጠመንጃ አድሏል፤ አንዳንዶችም እንዲዋጉ አስገድዷቸዋል፡፡ የአርሶ አደሩ ሰብል የወደመው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሕወሃት ከተሞችን ከመልቀቁ በፊት የመንግሥት ቢሮዎችን እና ሆስፒታሎችን ጭምር አውድሟል" ይላሉ አቶ ምንይችል፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከመንግሥት ጋር ትስስር ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቀደም ሲል ባወጣው ሪፖርት፣ በምዕራባዊ ትግራይ የሰፋፊ እርሻዎች ማዕከል በሆነችው ሑመራ፣ የአማራ ወጣት ቡድኖች፣ ሚሊሻ፣ ልዩ ሃይል እና የተወሰኑ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች የሕዝቡን ቤት ንብረት እንደዘረፉ ከነዋሪዎች መስማቱን ገልጧል፡፡
"ዘራፊዎቹ የምግብ እና ጥራጥሬ ማከማቻዎችን ባዶ አስቀርተዋቸዋል" በማለት የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ ሕዝቡን ለመርዳት የተላኩት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሃላፊዎችም በዘረፋው ስለመሳተፋቸው ባንድ የአካባቢው ነዋሪ ተነግሮኛል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት እና የአማራ ታጣቂዎች በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች መንግሥት ዕርዳታ እንዳከፋፈል የዐለማቀፉ ግጭት አጥኝ ቡድን ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ተንታኝ ዊሊያም ዴቪድሰን ይናገራል፡፡ የህወሃት ሃይሎች የጸጥታ ስጋት በሚደቅኑባቸው አካባቢዎች ግን ሕወሃት ዕርዳታውን ወርሶ ለራሱ እንዳይጠቀምበት ወይም ነዳጅ እና ጦር መሳሪያ እንዳያስገባ በመስጋት መንግሥት ዕርዳታ እያደረሰ አይደለም፡፡ "ባብዛኛው ገጠራማ አካባቢ የፌደራሉ መንግሥት ቁጥጥር አነስተኛ በመሆኑ ወይም የጸጥታ ችግር በመኖሩ ዕርዳታ አልደረሰም፡፡
የፌደራል ኃይሎች በደንብ ወደሚቆጣጠሯቸው የክልሉ ዋና ከተማ መቀሌ እና ወደ ምዕራባዊ እና ማዕከላዊ ትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች ግን ዕርዳታ እየተጓጓዘ ነው" ይላል ዴቪድሰን፡፡
'የኤርትራ ወታደሮች በቅድስቲቷ ከተማ'
ዴቪድሰን እንደሚለው፣ የኤርትራ ወታደሮች በግጭት ተሳታፊ ስለመሆናቸው መንግሥትም ሆነ ኤርትራ ስላላመኑ፣ የኤርትራ ወታደሮች ወደሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ዕርዳታ መላክ ከሎጅስቲክም ሆነ ከፖለቲካ አንጻር አስቸጋሪ ሊሆን ችሏል፡፡
የኤርትራ ወታደሮች ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያች ቅድስት ስፍራ በሆነችው አክሱም እና ከመቀሌ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምተገኘው ውቅሮ ከተሞች እንደሚንቀሳቀሱ የአካባቢው ሰዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡ ከሥልጣን የተወገዱት የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረጺዮን ገብረ ሚካዔል የትውልድ ከተማ በሆነችው ሽረ ግን፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከገቡ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች ወጥተዋል፡፡ ያም ሆኖ በከተማዋ አዋሳኝ የገጠር ቀበሌዎች አሁንም እንደሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
የሱዳን ቁልፍ ሚና
በሎንደን ዩኒቨርስቲ ኢንስቲትዩት ኦፍ ኮመንዌልዝ ስተዲስ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆነው ማርቲን ፕላውት እንደሚለው፣ መሬት መቆጣጠር የግድ የአሸናፊነት ማሳያ አይደለም፡፡
"ሕወሃት ትላልቅ እና ትናንሽ ከተሞችን ተቆጣጥሮ በመቆየት አያምንም ነበር፡፡ ጠላቶቹ እስከሚደላደሉ ይጠብቅና፣ ውጊያ የሚዋጋው ከኮረብታዎች እና ተራሮች ተነስቶ ነው፡፡
"ከዚያ ደፈጣ ጥሎ የመሰወር ስልት ነው የሚከተል፡፡ ጠላቱን በወራት ወይም ዐመታት ውስጥ ጨርሶ ያዳክማል፡፡ በቀደመው ሽምቅ ውጊያ ያደረገውም ይህንኑ ነው፡፡ ድጋሚ የተሳካ ሽምቅ ውጊያ ሊያደርግ የመቻሉ ነገር፣ የጦር መሳሪያ፣ ነዳጅ እና ምግብ አቅርቦት መስመሮችን በመቆጣጠሩ ወይም ባለመቆጣጠሩ የሚወሰን ይሆናል" ይላል ፕላውት፡፡
ድሮ ሕወሃት እነዚህን አቅርቦቶች የሚያገኘው ከሱዳን በኩል ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የድንበር ውጥረት እና ግጭት ውስጥ የገባችው ሱዳን፣ ድጋሚ ይህን ትፈቅዳለች ወይ? የሚለው ግን ከባድ ጥያቄ ነው- ይላል ፕላውት ሃሳቡን ሲያጠቃልል፡፡ "ጦርነቱ አጭር ወይስ የተራዘመ ይሆናል የሚለውን የምትወስነው ሱዳን ናት፡፡''








