ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ህንድ አርሶ አደሮች የረሃብ አድማ በመቱባቸው አካባቢዎች ኢንተርኔት አቋረጠች
ህንድ በቅርቡ የተሻሻለውን የግብርና ህግ በመቃወም አርሶ አደሮች የረሃብ አድማ እየመቱባቸው ባሉ አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ አድርጋለች።
አርሶ አደሮቹ በመዲናዋ ደልሂ ሶስት ቦታዎች ላይ ተቃውሟቸውን በረሃብ አድማ እየገለፁ ነው ተብሏል።
መንግሥት በበኩሉ "የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ" በሚል የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ እንዳደረገና ይኸም እስከ እሁድ ድረስ ይቀጥላል መባሉ ተገልጿል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደር ተቃዋሚዎች በህንዷ ደልሂ ከሰፈሩና ተቃውሟቸውን ማሰማት ከጀመሩ ከወር በላይ አስቆጥረዋል።
የአርሶ አደሮቹ የስራ ማህበራትና መንግሥት የሚያደርጉት ድርድር ያለ ፍሬ ተቋጭቷል ተብሏል።
በዚህ ሳምንት ማክሰኞች በተፈጠረ የትራክተር ትእይንት ግጭት ያስከተለ ሲሆን በዚህም አንድ ተቃዋሚ ሞቷል በርካታ ፖሊሶች ተጎድተዋል።
አንዳንድ ተቃዋሚዎች የደልሂ ታሪካዊ ቦታ የሚባለውን ሬድ ፎርትን ተቆጣጥረው የነበረ ሲሆን ፖሊስም በመግፋት ከአካባቢው እንዳስለቀቃቸው ተሰምቷል።
በትናንትናው ዕለት፣ ቅዳሜ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳሳወቀው አርሶ አደሮቹ የተሰባሰቡባቸው ሲንጉ፣ ጋዚፑርና ቲክሪ ግዛቶች ኢንተርኔት መቋረጡን አስታውቀዋል።
የአርሶ አደሮቹ መሪዎች በበኩላቸው የአንድ ቀኑ የረሃብ አድማ የታቀደው ህንዳውያን የነፃነት ታጋይ ብለው ከሚጠሩት ማህተመ ጋንዲ የሙት ዓመት መታሰቢያ ጋር ቀኑ እንዲገጥም ነው።
"የአርሶ አደሮች አንቅስቃሴ ሰላማዊ ነው፤ በሰላማዊነቱ ይቀጥላል" በማለት የህብረቱ መሪ ዳርሻን ፓል ተናግረዋል።
የኢንተርኔት መቋረጡ በርካታ ተቃዋሚዎችን እንዳበሳጫቸው ሮይተርስ በዘገባው አስነብቧል። ሳንዲ ሻርማ የተባለ አርሶ አደር ባለስልጣናቱ ፍርሃት ለመንዛት እየተጠቀሙበት እንደሆነ ሲናገር ሌላኛው ብሃቬሽ ያዳቭ የተባለ አርሶ አደር ደግሞ "ዲሞክራሲን" እየገደሉት ነው ብሏል።
አርሶ አደሮቹ ተቃውሞ የሚያደርጉባቸው አካባቢዎች መታወቁን ተከትሎ በተፈጠረ ውጥረት መንግሥት ኢንተርኔት ማቋረጡን አስታውቋል።
በያዝነው ሳምንት አርብ ማንነታቸው ያልተገለፁ ሰዎች ሲንጉ በሚባል አካባቢ አርሶ አደሮቹ ለቀው እንዲሄዱ መንገራቸውን ተከትሎ ግጭቶች ተነስተዋል ተብሏል።
አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት ግለሰቦች ድንጋይ ከመወርወር በተጨማሪ ድንኳኖቻቸውን ከጥቅም ውጭ እንዳደረጉት ተናግረዋል። በርካታ ሰዎችም ተጎድተዋል ተብሏል። የህንድ ሚዲያ እንደዘገበው ግለሰቦቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ሲሆኑ አርሶ አደሮቹን የከባቢውን ሰላም በመረበሽና ምጣኔ ኃብቱን ጉዳት ውስጥ ከታችኋል በማለት እየወነጀሏቸው ይገኛሉ።
አርሶ አደሮቹ አገሪቷ በቅርቡ የተሻሻለው ሕግ ከጥቅማችን የሚቃረን ነው ይሉታል።
በሕንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮና በድህነት ከሚኖሩ መካከል አርሶ አደሮች ዋነኞቹ ናቸው። ከዚህ ቀደም የመንግሥት ፖሊሲዎች በነፃ ገበያ እንዳይጎዱም ሲጠብቃቸው ነበር።
ያ ግን አሁን ተቀይሯል። አዲሱ ሕግ ኮርፖሬሽኖችንና ከፍተኛ ገንዘብ ያላቸውን የሚጠቅምና ደሃ አርሶ አደሮችን አዘቅት ውስጥ የሚከት ነው ይላሉ።
ከዚህ ቀደም መንግሥት የግብርና ዘርፉን ገበያውን ይቆጣጠረው የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ግን እሱ ቀርቶ አርሶ አደሮቹ በቀጥታ ከግል ሻጮች ጋር ዋጋ መደራደር ይችላሉ።
አዲሱ ሕግ ከዚህ ቀደም ነጋዴዎች እህል ማከማቸት በወንጀል ይቀጣ የነበረውን በማሻሻል ማከማቸት ይችላሉ ይላል።
በዚህም በወረርሽኝ ወቅት ነጋዴዎች ዋጋ እንዲጨምሩ የሚያስችል ዕድል ሰጥቷል።
በሕንድ ከ86 በመቶ በላይ የሚሆኑት አርሶ አደሮች አነስተኛ መሬት ወይም ከሁለት ሄክታር በታች ያላቸው ናቸው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ በሆነበት ሁኔታ ጠቀም ባለና ለኑሯቸው በሚሆን ዋጋ ምርታቸውን ለትልልቅ ኩባንያዎች ለመሸጥ የመደራደሪያ አቅሙ የለንም ይላሉ።
የግሉ ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ የዘርና የማዳበሪያን ዋጋ በመጨመር ኑሯቸውን ከባድ አድርጎታል።
ከዚህ ቀደም መንግሥት ዝቅተኛ የዋጋ ድጋፍ የሚል ፖሊሲ የነበረው ሲሆን መንግሥት ሩዝና ስንዴ ለሚያመርቱ አምራቾች የሚሰጠው የዋጋ ነበረው።
በአዲሱም ሕግ ይህንንም ድጋፍ ያጣሉ ተብሏል።
መንግሥት በበኩሉ የግል ተቋማትን በግብርና ዘርፉ እንዲሳተፉ የፈቀደው ይህ ማሻሻያ አርሶ አደሮችን አይጎዳም በማለት ይከራከራል።
ይህ ግን ከአርሶ አደሮቹ ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም። አርሶ አደሮቹን ሳያሳትፍ የወጣ ሕግ ነው በሚል አመፁን አቀጣጥሎታል።