ትግራይ ፡ የነዋሪዎችና የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ ወደ ሰብአዊ ቀውስ ሊያመራ ይችላል፡ ኢሰመኮ

ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ደኅንነትና ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንና የሰብአዊ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ።

ኮሚሽኑ ይህንን ያለው ወደ ትግራይ ክልልና አንዳንድ የአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በመጓዝ የችግሩ ተጠቂዎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር አገኘሁት ባለው መረጃ በመመስረት ባወጠው ሪፖርት ላይ ነው።

ኢሰመኮ በተመለከታቸው በዳንሻ፣ በሁመራ፣ በቢሶበርና በኡላጋ የተካሄደው ጦርነት የሠላማዊ ሰዎች ሞትና አካላዊ ጉዳት፣ የመኖሪያና የንግድ ቦታዎች ዝርፊያና የተለያዩ ጉዳቶች አስከትሏል።

በዚህም በቢሶበርና በኡላጋ 31 ሠላማዊ ሰዎች ሲሞቱ፤ 104 መኖሪያ ቤቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ሲቃጠሉ የአካባቢው ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።

በተጨማሪም በመሰረተ ልማቶች ላይ ውድመት የደረሰ ሲሆን የኤሌክትሪክ፣ የውሃና የመሳሰሉ አገልግሎቶች መልሰው ሥራ አለመጀመራቸው በነዋሪዎችና በተፈናቃናዮች ላይ የበለጠ ሰብአዊ ቀውስ እንዳያስከትል የሚያሰጋ ነው።

በተመሳሳይ መልኩ በሁመራና በዳንሻ የሠላማዊ ነዋሪዎች ንብረት የሆኑ የመኖሪያና ንግድ ቤቶችን ጨምሮ የአካባቢው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ውድመትና ዝርፊያ መፈጸሙን ኮሚሽኑ ገልጿል።

"ሠላማዊ ነዋሪዎች በብሔራቸው ምክንያት ወይም በአካባቢዎቹ የፀጥታ መጓደል ምክንያት ለደኅንነታቸው እንደሚሰጉ" ለኮሚሽኑ ገልጸዋል።

"በአጠቃላይ በእነዚህ አራት ከተሞች ያለው የፀጥታ ስጋትና የፍትሕ አካላት ወደ መደበኛ ሥራቸው አለመመለስ፣ የሰዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅና የሰብአዊ መብቶቻቸውን ጥበቃ ለማረጋገጥ አዳጋች አድርጎታል" ብሏል ኢሰመኮ።

"በአካባቢዎቹ ያለው የፀጥታ ሁኔታ፣ የነዋሪዎቹንም ሆነ ከትግራይ ክልል ወደ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎችን የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት እንዲጨምርና የመቋቋም አቅማቸውን በአስከፊ ሁኔታ እንዲፈተን አድርጓል" ሲሉ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ ጨምረውም የችግሩ ተጎጂዎች በቂ ያልሆነ ወይም ምንም እርዳታ እንዳላገኙ ገልጸው "በአካባቢዎቹና በሠላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛና አፋጣኝ ርብርብ የሚጠይቅ ነው" በማለት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አሁን በተወሰኑ አካባቢዎች ካደረጋቸው ምልከታዎች በተጨማሪ ለመስክ ምልከታ ወደ መቀለ ከተማና ወደ ሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች በመንቀሳቀስ፣ በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረውን የሰብአዊ ቀውስና የሰብአዊ መብት ጉዳዮች በመመርመር ላይ እንደሚገኝና ሥራው ሲጠናቀቅ ተጨማሪ ሪፖርት እንደሚያወጣ ገልጿል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ በርካታ ሰዎች ለአካል ጉዳትና ለመፈናቀል የተዳረጉ መሆናቸው ቢገለጽም ትክክለኛው አሃዝን በተመለከተ የሚታወቅ ነገር የለም።

በግጭቱ የመጀመሪያ ሰሞን ከ50 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን መሰደዳቸው የተነገረ ሲሆን፤ በአገር ውስጥ ተፈናቅለው የሚገኙ ሰዎች ደግሞ ከዚህ በብዙ ሺህ እንደሚበልጥ የተራድኦ ድርጅቶች ይገምታሉ።

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ባለው ጊዜ ውስጥ የሰብአዊ እርዳታ በአስፈላጊው መጠን መቅረብ ካልቻለ የረሃብ አደጋና የከፋ ችግር ሊከሰት እንደሚችል እየተነገረ ሲሆን፤ መንግሥትና እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በአፋጣኝ የሰብአዊ እርዳታ እንዲያቀርቡ ጥሪ እየቀረበላቸው ነው።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም በሪፖርቱ በዳሰሳቸው አካባቢዎች ያለው የነዋሪዎች ሁኔታ ወደ ሰብአዊ ቀውስ ሊያመራ ስለሚችል የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቋል።

በተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰውና የክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል እንደሚለው በትግራይ ክልል 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል።