ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንበጣ ወረራ ፡ በምስራቅ አፍሪካ አዲስ የአንበጣ ወረራ ስጋት እንዳለ ፋኦ አስጠነቀቀ
በደቡብ ኢትዮጵያና በሰሜን ኬንያ የተከሰተው አዲስ የአንበጣ መንጋ በምሥራቃዊ አፍሪካ አካባቢዎች እየተዛመተ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት [ፋኦ] አስጠነቀቀ።
ድርጅቱ ሰኞ ዕለት ባወጣው መረጃ፤ አዲስ የተፈለፈሉ የአንበጣ መንጋዎች ከዚህ ቀደም ከተከሰተባቸው ምሥራቅ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ሶማሊያ በመሰደድ ወደ ኢትዮጵያ ደቡብ ክልል እና ወደ ሰሜን ኬንያ እና የባህር ዳርቻዎች አካባቢ እየተስፋፋ ነው ብሏል።
እስካሁን ድረስ በአራት የኬንያ ግዛቶች ማለትም በዋጂር፣ ጋሪሳ፣ ማርሳቢት እና በቅርቡ ደግሞ ኢሲኦሎ ግዛቶች የአንበጣ መንጋው መከሰቱን ድርጅቱ ጠቅሷል።
"የአንበጣ መንጋው መራባቱን ቀጥሏል። በኬንያ ደቡብ ምስራቅ ታይታ ታቬታ እና በባህር ዳርቻዎች አካባቢ ደግሞ እድገቱን ያልጨረሰ የአንበጣ መንጋ ይገኛል" ብሏል ድርጅቱ።
የተወሰነው የአንበጣ መንጋ በዚህ ወር ወደ ሌሎች የኬንያ አካባቢዎች እንዲሁም ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳ ሊደርስ እንደሚችል ድርጅቱ አስጠንቅቋል።
የአንበጣ ወረራ በቀጠናው ለምግብ ዋስትና ትልቅ ስጋት መሆኑን የጠቀሰው ድርጅቱ፤ ባለፈው ዓመት በቀጠናው የተከሰቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ አንበጣዎች በሰብል ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጿል።
በመሆኑም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቱ፤ አገራት ጥናት ለማካሄድ፣ የአንበጣ መንጋውን ፍልሰት ለመቀነስ እና የነፍሳቱን እርባታ ለመቆጣጠር አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ድርጅቱ አክሎም የአንበጣ መንጋው በማዕከላዊ ኬንያ ምን አልባትም ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ ታንዛኒያ፣ ምስራቃዊ ኡጋንዳ እና በደቡብ ምስራቅ ደቡብ ሱዳን በተያዘው ወር ሊደርስ እንደሚችል ትንበያውን አስቀምጧል።
በሰሜን ምሥራቅ ታንዛኒያ ምዋንጋ አካባቢ እድገቱን ያልጨረሰ የአንበጣ መንጋ መታየቱን ሪፖርቶች እንደሚያመልክቱ ድርጅቱ ገልጿል።
"የአንበጣ መንጋ የሚመቸው ቦታ ላይ ከደረሰ፤ በማደግ፣ እንቁላል በመጣልና በመፈልፈል በየካቲትና መጋቢት ወር ላይ እድገቱን ያልጨረሰ የአንበጣ መንጋ ይፈጠራል" ሲል አሳስቧል ድርጅቱ።
በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል።