ሴቶች በካቶሊክ ቤተክርስቲያን አገልግሎት እንዲያካሂዱ ፖፕ ፍራንሲስ ፈቀዱ

ፖፕ ፍራንሲስ ከሰሞኑ የሮማውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ህግ በመቀየር ሴቶች ቁርባንን ጨምሮ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኗን አገልግሎቶችን እንዲያካሂዱ ፈቅደዋል።

በተቀየረው ህግም መሰረት ሴቶች ቤተ መቅደሱ ውስጥ ሆነው ማገልገልም ይችላሉ።

ሆኖም የተቀቡት ቄስ በበላይነት ስርዓቱን እንደሚቆጣጠሩ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በተለያዩ በምዕራባውያን አገራት በሚገኙ የካቶሊክ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ ሴቶች እነዚህን አገልግሎቶች የሚያከናውኑ ሲሆን የፖፑ የአሁኑ ውሳኔ ለነዚህ ስፍራዎች እውቅናን እንዲያገኙ ሆኗቸዋል።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የበላይ ተቆጣጣሪ ፖፕ ፍራንሲስ እንዳሉት ሴቶች በቤተክርስቲያኗ ላይ "ለየት ያለ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው" ብለዋል።

የአሁኑም ውሳኔ ወግ አጥባቂ የሚባሉ የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎችን ሴቶች በቤተ ክርስቲያኗ ባለው የአምልኮ ስርአትም ያላቸውን ሚና ከፍ እንዲያደርጉም ያስገድዳቸዋል ተብሏል።

ፖፑ ቤተክርስቲያኗ ሁሉንም ትቀበላለች የሚለውንም ለማሳየት የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረጉ መሆናቸውን የቢቢሲው ማርክ ሎወን ከሮም ዘግቧል።

ነገር ግን ባለፈው አመት ሴቶች አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎትን ያከናውኑ ዘንድ ዲያቆን መሆን ይችላሉ ወይ የሚለውን በተመለከተ ውሳኔ ለማስተላለፍ ሲኖዶሱ በተዘጋጀበት ወቅት ፖፑ ህጉ አይቀየርም በማለት በእምቢተኝነት ፀንተዋል።

መሰረታዊ የሚባሉ ማሻሻያዎችን ከቤተ ክርስቲያኗ ሲጠብቁ የነበሩትንም አካላት ውሳኔያቸው ተስፋ አስቆርጠዋል።

በአሁኑ ወቅት ፖፑ የቀየሩት ሃረግ "ማንኛውም ወንድ" የሚለውን "በማንኛውም ሰው" በሚል እንዲተካ አድርገዋል።

በዚህም መሰረት ሴቶች በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ባሉ የአምልኮ ስርአቶች ሴቶች ቅዱሳት መፃህፍትን ያነባሉ እንዲሁም በቅዳሴ ወቅትም ረዳት መሆን ይችላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ በቅዳሴ ወቅት ሴቶቹ ቁርባን ማቁረብ እንዲሁም ፀሎቶችን ማድረስና ሌሎች አገልግሎቶች የማከናወን ሚና ይኖራቸዋል።