ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ በእንግሊዝ ሆስፒታሎች እየተጨናነቁ ነው
በደቡባዊ እንግሊዝ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ሆስፒታሎች እየተጨነናነቁ መሆኑ ተገልጿል።
ያሳለፍነው ቅዳሜ ደግሞ በለንደን የአምቡላንስ አገልግሎት ታሪክ ውስጥ እጅግ ስራ የበዛበት ቀን ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ አዲሱ የኮሮናቫይረስ አይነት እንደሆነ ተገልጿል።
የአምቡላንስ አገልግሎት ሰጪውና ሌሎች ተጨማሪ ሁለት የድንገተኛ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፤ ሰዎች በጣም አሳሳቢ የጤና እክል ካልገጠማቸው የአደጋ ጊዜ ቁጥር ወደሆነው 999 እንዳይደውሉ ጭምር እስከማሳሰብ አድርሷቸዋል።
የድንገተኛ ህክምና ኮሌጅ ፕሬዝደንት የሆኑት ዶክተር ካትሪን ሄንደርሰን አንድ ለንደን ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ሁሉም ታማሚዎች የኮሮናቫይረስ ህሙማን መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቷ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ''በአሁኑ ሰአት ነገሮች በጣም አስቸጋሪ ናቸው። በገና በአል ሳምንት ይህን ያክል ቁጥር ያለው ታማሚ ማስተናገድ አዳጋች ነው'' ብለዋል።
አክለውም ''በአሁኑ ሰአት በርካታ ታማሚዎች እያስተናገድን ነው፤ ነገር ግን ሁሉም የሚያስፈልጋቸውን የተሟላ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ላይ የቻልነውን ሁሉ እያደረግን ነው'' ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የስኮትላንድ የጤና ስርአት ከአቅሙ በላይ ታካሚዎችን እያስተናገደ እንደሆነ ዶክተሮች የገለጹ ሲሆን፤ አንዳንድ ሆስፒታሎች የኮቪድ-19 ታካሚዎችን ለመርዳት የሚያስችል ድጋፍ ጠይቀዋል።
የግላስኮው ሕክምና ባለሙያዎች ኮሌጅ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ጃኪ ታይለር በበኩላቸው በአሁኑ ሰአት በደቡባዊ እንግሊዝ እየታየ ያለው ሁኔታ ስኮትላንድ ውስጥ ባሳለፍነው ሕዳር ወር ላይ ከተከተሰተው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።
''እስካሁኑ ሰአት ድረስ እንኳን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኮቪድ-19 ታማሚዎች ወደ ሆስፒታሎች እየመጡ ሲሆን አብዛኛዎቻቸው የመተንፈሻ አካላት እክል ያጋጥማቸዋል'' ብለዋል።
እሁድ ዕለት በዩናይትድ ኪንግደም 30 ሺህ 501 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፤ 316 ሰዎች ደግሞ በዚሁ ቫይረስ የተነሳ ሕይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።
ነገር ግን ስኮትላንድ ባለፉት አራት ቀናት በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ቁጥር አለመግለጿ እና ኖርዘርን አየርላንድ የሚያዙትንም ሆነ የሚሞቱን ሰዎች ቁጥር አለመግለጿ አጠቃላይ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል አስገምቷል።
ከሳምንት በፊት በመላው ዩናይትድ ኪንግደም 21 ሺህ 286 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘው ሆስፒታል መግባታቸውም ተገልጿል።
እሁድ ዕለት ቢቢሲ የተመለከተው ሰነድ ላይ የድንገተኛ ክፍል ሰራተኞችና የአምቡላንስ አገልግሎት ሰጪዎች የኮሮናቫይረስ ታማሚዎችን ለሆስፒታል ሰራተኞች ለማስረከብ እስከ ስድስት ሰአት ድረስ ፈጅቶባቸው ነበር።
አንድ የድንገተኛ ክፍል ሰራተኛ ለቢቢሲ ሲናገር ''አንዳንድ ታማሚዎች አምቡላንስ ውስጥ ጭምር ህክምና ተደርጎላቸዋል። ምክንያቱም ሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኙት አልጋዎች ሞልተው ነበር'' ብሏል።