የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ከ20ሺህ ዶላር በላይ ሆነ

ቢትኮይን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቢትኮይን በዚህ ዓመት ዋጋው በ170 በመቶ ከፍ በማለት የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ከ20 ሺህ ዶላር በላይ ሆነ።

ይህ ቨርቿል ከረንሲ ዋጋው የጨመረው የድርሻ ገበያዎች እየተንኮታኮቱ በሚገኙበት ወቅት ነው።

ትናንት ዋጋው በ4.5 በመቶ በመጨመር አንድ የቢትኮይን ዋጋ 20 ሺህ 440 ሆኖ ነበር።

ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ የሚዋዥቀው ይህ ዲጂታል ከረንሲ እአአ 2017 ላይም በተመሳሳይ ዋጋው በከፍተኛ ፍጥነት ጨምሮ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ከ20 ሺህ ዶላር ለመሻገር ተቃርቦ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዲጂታል ከረንሲው ከዚህ ቀደም ዋጋው በአስደንጋጭ መጠን ወርዶ እስከ 3ሺህ 300 ዶላር ድረስ ተገምቶ ነበር።

እንደ ማይክሮሶፍት፣ ስታርባክስ እና ፔይፓል ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ዲጅታል ከረንሲውን ለግብይት መጠቀም መጀመራቸው የቢትኮይን ዋጋ ሊጠናከረው እንደሚችል ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ቢትኮይን ግብይት ለመፈጸም መዋል የለበትም የሚሉ አሉ። የባንክ ኦፍ ኢንግላንድ ገዢ አንድሪው ቢሊ የቢትኮይን ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ከፍ እና ዝቅ ስለሚል ሰዎች ዲጂታል ከረንሲውን ለግብይት መጠቀማቸው እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል።

ቢትኮይን እአአ 2009 ላይ ከተፈጠረ ወዲህ በአማካይ እድገትን ሲያሳይ ቆይቷል። በዚህ ዓመት ደግሞ ዋጋው ታይቶ የማይታወቅ ጣሪያን ነክቷል። 'ኮምፒቲቲቭ ኮምፕሊያንስ' የተሰኘ አማካሪ ድርጅት መስራች የሆኑት ያና አፍናሲዬቫ የቢትኮይን ዋጋ በቀጣይ ወራትም ሊጨምር እና ሊቀንስ ይችላል ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት በርካታ አይነት ክሪፕቶካረንሲዎች (ዲጂታል ገንዘቦች) አሉ። በስፋት ከሚታወቁት መካከል አንዱ ቢትኮይን ነው።

ቢትኮይን ማለት በቀላል ቋንቋ፤ ዲጂታል+ገንዘብ+መገበያያ በማለት ማጠቃለል ይቻላል። ይህ መገበያያ በኪሳችን ተሸክመን እንደምንዞረው የብር ኖት ወይም ሳንቲም ሳይሆን 'ኦንላይን' የሚቀመጥ ዲጂታል ገንዘብ ነው።

ሌላው የቢትኮይንና የተቀሩት የክሪይፕቶከረንሲዎች ልዩ ባህሪ በመንግሥታት እና በባንኮች አለመታተማቸው እንዲሁም ቁጥጥር አለመደረጉ ነው። ቢትኮይን የሚፈጠረው 'ማይኒንግ' በሚባል ሂደት ነው።

በመላው ዓለም በኔትወርክ በተሳሰሩ ኮምፒውተሮች ቁጥጥር ይደረግበታል።

ባለፉት ዓመታት ዋጋ በፍጥነት ሲጨምር ለዋጋው መጨመር ምክንያቱ በትክክል ይህ ነው ማለት አልተቻለም። አንዳንድ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ግን ኢንቨስተሮች ''እድሉ እንዳያልፋቸው'' ከሚገባው በላይ ፈሰስ እያደረጉበት ነው የሚል ምክንያት ያቀርባሉ።

ሌሎች ደግሞ የቢትኮይን ተቀባይነት እየጨመረ በመምጣቱ ዋጋው እንደጨመረ ያስቀምጣሉ።

ቢትኮይን እንደ ስጋት?

አሸረትስ በተባለ የፋይናንስ ተቆጣጣሪ ኩባንያ ውስጥ ባለሙያ የሆኑት ብራደሊይ ራይስ በቢትኮይን ላይ ምንም አይነት ቁጥጥር እንደማይደረግበት ያስታውሳሉ።

ቢትኮይንን በመጠቀም የገዢው ማንነት ይፋ ሳይደረግ በየትኛውም ሰዓት እና በየትኛውም ስፍራ የቢትኮይን ዝውውር ማድረግ ይቻላል። የግዢው ማንነት ይፋ ሳይደረግ ግብይት መፈጸም ይቻላል።

በዚህም ሕገ-ወጥ ቡድኖች የጦር መሳሪያዎች እና እጾችን ሊገዙ እና ሊሽጡ ይቻላሉ፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና አሸባሪዎችን ለመደገፍ ያስችላል በማለት ቢትኮይንን ጨምሮ ሌሎች ክሪይፕቶከረንሲዎች ላይ ያላቸውን ስጋት የሚያነሱ በርካቶች ናቸው።