የትራምፕ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር 'ጆ ባይደን እንኳን ደስ አለዎት' አሉ

የዶናልድ ትራምፕ ሪፐብሊካን ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑትና ከፍተኛ ደምጽ ያለው የሴኔቱ መሪው ሚች ማክኮኔል ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባሳለፍነው ወር ለተቀዳጁት ድል የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሴናተር ማክኮኔል ኢሎክቶራል ኮሌጁ በይፋ ጆ ባይደን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ማረጋገጡን ተከትሎ ነው ንግግር ያደረጉት።

ዴሞክራቱ ባይደን ከኢሌክቶራል ኮሌጁ 306 ድምጽ ያገኙ ሲሆን ተቀናቃኛቸው ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ 232 ድምጽ ማግኘታቸው ተረጋግጧል።

ተመራጩ ፕሬዝደንት ጀ ባይደን በሪፐብሊካኖች የበላይነት በሚታይበት የሴኔት ምክር ቤት ከሪፐብሊካኖች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ወደፊት የሚኖራቸው አስተዳደር ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይገመታል።

ባይደን በሚቀጥለው ወር በሚካሄደው ምርጫ ዴሞክራቶች ድምጽ እንዲያገኙ አትላንታ እና ጆርጂያ በመሄድ ቅስቀሳ አድርገዋል።

ሁለት የሴኔቱ መቀመጫዎች በሚቀጥለው ወር የሚወሰኑ ሲሆን ውጤቱ ጆ ባይደን ፓርቲያቸው ሴኔቱን ይቆጣጠራል ወይስ አይቆጣጠርም የሚለውን ይወስናል።

ዴሞክራቶች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን ተቆጣጥረውታል።

ሰኞ ዕለት ጆ ባይደን በይፋ ፕሬዝደንት መሆናቸው ከታወጀ በኋላ እስካሁን ሶስት የዓለም መሪዎች እንኳን ደስ አለዎት የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

እንኳን ደስ አለዎት ያሉት መሪዎች የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ዣዬር ቦልሶናሮ እና የሜክሲኮው ፕሬዝዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ ናቸው።

በሴኔቱ ቀርበው ንግግር ያደረጉት ሚች ማክኮኔል ውጤቱ የተለየ ነገር ይዞ ቢመጣ ብለው ተስፋ አድርገው እንደነበርና ኢሌክቶራል ኮሌጁ ይፋ ያደረገውን ውጤት ግን እንደሚቀበሉ ገልጸዋል።

''ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንን እንኳን ደስ አለዎት ማለት እፈልጋለው'' ሲሉ ንግግር አድርገዋል።

በተጨማሪም ሚች ማክኮኔል ለካማላ ሃሪስም የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ''ሁሉም አሜሪካውያን አገራችን በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት ስላገኘች ሊኮሩ ይገባል'' ብለዋል።

ከቆይታ በኋላ ደግሞ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሴናተር ሚች ማክኮኔል ጋር ስልክ በመደወል ለእንኳን ደስ አለዎት መልዕክቱ ምስጋናቸውን እንዳቀረቡና በቅርቡም ተገናነኝተው እንደሚወያዩ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ካማላ ሀሪስ በበኩላቸው ከኤቢሲ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሴናተሩን መልዕክት እንደሚቀበሉት በመግለጽ ''ቀደም ብለው መልዕክታቸውን ቢያስተላልፉ መልካም ነበር ነገር ግን ዋናው መልዕክቱ መተላለፉ ነው። ወደፊት መጓዝ አለብን። ሁላችንም የምንስማማበት አላማ ካገኘን ተባብረን እንስራው'' ብለዋል።