ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ እስካሁን ባልታየ መጠን የካርቦን ልቀትን ቀነሰ
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተወሰዱ እርምጃዎች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአየር ብክለት እንዲቀንስ ማገዛቸው ተገለጸ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት የቀነሰው ዘንድሮ ነው። የልቀት መጠኑ 7% ቀንሷል።
ዝቅተኛ የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት ያስመዘገቡት ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ናቸው።
የወረርሽኙን ሁለተኛ ዙር ስርጭት ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣላቸው ነው የአየር ብክለትን መቀነስ የቻሉት።
ከወረርሽኙ ያገገመችው ቻይና ግን በቀጣዩ ዓመት የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀቷ እንደሚጨምር ተገልጿል።
“ግሎባል ካርቦን ፕሮጀክት” እንዳለው፤ ዘንድሮ የካርቦን ልቀት ወደ 2.4 ቢሊዮን ቶን ወርዷል።
እአአ 2009 ላይ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ሲከሰት የካርቦን ልቀት የቀነሰው በግማሽ ብቻ ነበር።
በያዝነው ዓመት አሜሪካ እና አውሮፓ 12% ቀንሰዋል።
ከፍተኛ መቀነስ የተስተዋለው በፈረንሳይ (15%) በዩናይትድ ኪንግደም (13%) ነው።
የዩኬው ፕ/ር ኮርኒ ለኩዌሬ “የሁለቱ አገሮች የካርቦን ልቀት ዋነኛ ምንጭ የመጓጓዣ ዘርፍ ነው። ኢንዱስትሪ እናሌሎች ዘርፎች በሁለተኛ ደረጃ ይገኛሉ” ይላሉ።
በመላው ዓለም በወረርሽኙ ሳቢያ የበረራ ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል። ይህም ለካርቦን ልቀት መቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
ከዚህ ዘርፍ የሚመዘገበው የካርቦን ልቀት 40% ሲሆን ይህም ከአምናው ያንሳል።
ስለዘንድሮው የካርቦን ልቀት መጠን ጥናት የሠሩት ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ቻይና በዚህ ዓመት የካርቦን ልቀቷን በ1.7% ቀንሳለች።
ሆኖም ግን ባለፉት ጥቂት ወራት የወረርሽኙን ስርጭት በተሻለ ሁኔታ መቆጣጠሯ የካርቦን ልቀት ዳግመኛ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።
የጥናቱ ተሳታፊ ጃን አይቨር ኮርስባክን እንዳሉት፤ እአአ በ2020 መጨረሻ ላይ የቻይና የካርቦን ልቀት ከ2019 ጋር ተቀራራቢ ነው።
“አንዲያውም አንዳንድ መላ ምቶች እንደሚጠቁሙት የቻይና የካርቦን ልቀት እየጨመረ ሳይመጣ አይቀርም” ብለዋል አጥኚው።
የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት ላይ የተቀመጠው ግብ እንዲሳካ ለቀጣይ 10 ዓመታት፤ በየዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ቶን የካርቦን ልቀት መቀነስ እንዳለበት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ፕ/ር ፒዬሬ ፍሪድልግስተን እንደሚሉት፤ የዓለም አየር ንብረት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊስተካከል የሚችለው የካርቦን ልቀት ዜሮ ሲደርስ ነው።