ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መረጃ ሰርሳሪዎች የኮቪድ-19 ክትባት ዝውውርን ለማደናቀፍ አሲረዋል?
ዓለም አቀፉ የኮቪድ-19 ክትባት ዝውውር መስመር በኮምፒውተር መረጃ ሰርሳሪዎች ኢላማ መደረጉን የአሜሪካው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋም አይቢኤም አስታውቋል።
ኢላማ የተደረገው ክትባቶች ሲጓጓዙ በቀዝቃዛ ቦታ እንዲቀመጡ የሚያስችለው መሣሪያ ነው።
መረጃ ሰርሳሪዎቹ እነማን እንደሆኑ ባይታወቅም፤ ለምዝበራ የተጠቀሙት መንገድ የተራቀቀ መሆኑ ምናልባትም ከምዝበራው ጀርባ ያሉት አገራት ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላክቷል።
ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች የኮቪድ-19 ክትባት ምርምር በመረጃ ሰርሳሪዎች ኢላማ ተደርጓል ብለው ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ይታወሳል።
የተጭበረበሩ ኢሜሎች
አይቢኤም እንደሚለው፤ መረጃ ሰርሳሪዎቹ እንቅስቃሴ የጀመሩት መስከረም ላይ ነው።
ሐሰተኛ ኢሜሎች በስድስት አገሮች ለሚገኙ ተቋሞች ተልከዋል። ተቋሞቹ ጋቪ በመባል ከሚታወቀው ዓለም አቀፍ የክትባት አምራቾች ጥምረት ጋር ትስስር ያላቸው ናቸው።
ከጥምረቱ አባሎች መካከል የዓለም ጤና ድርጅት፣ ዩኒሴፍ፣ የዓለም ባንክ እንዲሁም የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ይገኝበታል።
እነዚህ ድርጅቶች ክትባት በድሃ አገሮች እንዲደርስ የሚሠሩ ናቸው።
ክትባቶች ሳይበላሹ ከቦታ ቦታ እንዲጓጓዙ ለማስቻል ‘ኮልድ ቼን’ የተባለ ቀዝቃዛ መሣሪያ እንዲሁም ሂደት አለ። መረጃ መዝባሪዎች ኢላማ ያደረጉትም ይህንን ነው።
የመረጃ ሰርሳሪዎቹ መረብ
የፋይዘር እና ባዮቴክ ክትባቶች ሲጓጓዙ ከዜሮ በታች በ70 ሴንቲ ግሬድ መቀመጥ አለባቸው።
መረጃ ሰርሳሪዎቹ ኢሜል የሚልኩት አንድ የቻይና የንግድ ተቋም ዋና ኃላፊን አስመስለው ሲሆን፤ ተቋሙ በክትባት ዝውውሩ ተሳታፊ ከሆኑ አንዱ ነው።
ኢሜሉ የተላከው ለመጓጓዣ ድርጅቶች ሲሆን፤ ሐሰተኛ ኮዶች በውስጡ ይዟል።
ኢሜሉን የሚመልሱ ድርጅቶች በሚሰጡት መረጃ አማካይነት ክትባቶችን እንዴት ለማዘዋወር እንደታቀደ ማወቅ ይቻላል።
አይቢኤም እንደሚለው፤ መረጃ ሰርሳሪዎቹ ክትባቶችን ለማዘዋወር የወጣውን ውጥን ካወቁ በኋላ ጥቃት ይሰነዝራሉ።
ጥቃቱ ካነጣጠረባቸው መካከል የአውሮፓ ኮሚሽን የግብር ድርጅት ዋና ኃላፊ እና ከጸሐይ ኃይል የሚያመነጭ መሣሪያ የሚያመርቱ ተቋሞች ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ተቋሞች የሚሠሩት መሣሪያ ክትባቶችን ቀዝቃዛ ቦታ ለማስቀመጥ ያስችላል።
የደቡብ ኮርያ መተግበሪያ አምራች እና የጀርመን ድረ ገጽ አምራች ሌሎቹ የጥቃቱ ኢላማ ናቸው።
ድረ ገጽ አምራቹ ለመድኃኒት ሠሪዎች፣ አጓጓዦች እና ሌሎችም ድጋፍ ይሰጣል።
ጥቃቱ እንዴት ታወቀ?
አይቢኤም ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የሚሰነዘሩ የኮምፒውተር መረጃ ምዝበራዎችን ለማምከን የደህንት ቡድን አዋቅሮ ነበር።
የኮቪድ-19 ክትባት ዝውውር መስመር በኮምፒውተር መረጃ ሰርሳሪዎች ኢላማ መደረጉን የደረሰበትም በዚህ ቡድን አማካይነት ነው።
“መረጃ መዝባሪዎቹን የሚደግፉ አገራት ባይኖሩ ከፍተኛ ጊዜና ገንዘብ አውጥተው ጥቃቱን አይወጥኑም ነበር” ብሏል አይቢኤም ባወጣው መግለጫ።
አይቢኤም የምዝበራው ኢላማ ለተደረጉ ድርጅቶችና ለጸጥታ ኃይሎች መረጃውን አቀብሏል።
የአሜሪካ የሳይበር ደህንነት ኤጀንሲ ጥቃቱን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል። በማስጠንቀቂያው ክትባት አጓጓዥ ድርጅቶች ጥበቃ እንዲደረግላቸው አሳስቧል።
ሐምሌ ላይ ዩናይትድ ኪንግደም፤ ኦክስፎርድ የሚሠራውን ክትባት ሩስያ ኢላማ አድጋለች ስትል ከሳ ነበር።
አሜሪካ ደግሞ ቻይና መረጃ ለመመዝበር እየሞከረች ነው ማለቷ አይዘነጋም።
በተያያዥ፤ ሰሜን ኮርያ እና ሩስያ የኮቪድ-19 ክትባት ምርምርን ሊሰርቁ እንደነበር ማይክሮሶፍት በቅርቡ አስታውቋል።