ኬንያ ለማበጣበጥ እያሴረችብኝ ነው ስትል ሶማሊያ ወነጀለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኬንያ ሶማሊያን ለማበጣበጥና መረጋጋት እንዳይሰፍን እያሴረች ነው ሲሉ የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስትር ኦስማን አቡበከር ዱቤ ወቅሰዋል።
አገሪቷ ለምርጫ በምትዘጋጅበት ወቅትም ይህ እቅድ እየተከወነ እንደሆነም ሚኒስትሩ በአገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
"ኬንያን እናከብራለን። በጉርብትና የተመሰረተ አብሮነትና መተጋገዝም እንዲኖር እንፈልጋለን። በኛ በኩል እነዚህን እሴቶች አጠንክረን ይዘናል። ከኬንያ በኩል ግን በማይገባ የቀን ህልም እየቃበዙ የሶማሊያን መሬትና ውሃ መቆጣጠር ይፈልጋሉ" በማለትም በብሄራዊ ቴሌቪዥኑ ፌስቡክ ገፅ በቀጥታ በተላለፈ ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ እንደ አባሪ ያነሱትም ከኬንያ በኩል ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትና የሶማሊያ ተቃዋሚ መሪዎችን ናይሮቢ ማስተናገዷን በማንሳት ነው።
ከደቡባዊ ሶማሊያ ጁባላንድ ግዛት የተውጣጡ ፖለቲከኞች በመጪው የሶማሊያ ምርጫ ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ከዚህ ቀደምም እንዲሁ ፖለቲከኞቹ ውይይት አድርገዋል ተብሏል።
"ሞቃዲሾ አንድም ቢሆን የኬንያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን አስተናግዳ አታውቅም። በጎረቤቶቻችን ላይ ውጥረት እንዲነግስም አንፈልግም ነገር ግን በሶማሊያ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች መነሻቸው ከናይሮቢ ሆኗል።
በሶማሊያ የሚደረሱ ስምምነቶች የሚጣሱበትም ቦታ ኬንያ ሆኗል" ያሉት ሚኒስትሩ አክለውም
"በአገሪቱ ያለውን አገዛዝ ላይ አለመረጋጋትና ፖለቲካዊ ውጥረቶች እንዲነግሱ እቅዶች የሚቆመሩበት ቦታ ሆኗል-ናይሮቢ። ለዚያም ነው ለምክክር አምባሳደራችንን ከናይሮቢ የጠራነው" በማለት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ኬንያ በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ስር በሶማሊያ ያሰማራቻቸውን ወታደሮቿን ማስወጣቷን ተከትሎ ቁልፍ የሚባሉ ግዛቶቿ በአልሻበባብ ቁጥጥር ስር እንደዋሉም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
"በሶማሊያ የተሰማራው የኬንያ ኃይል ማንንም ሳያሳውቅ መውጣቱን ተከትሎ ግዛቶቹ በአልሻባብ ቁጥጥር ስር ውለዋል። ይህንን ችላ የምንለው ጉዳይ ሊሆን ይገባል?" ብለውም ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።
ከቀናት በፊት የሶማሊያ መንግሥት አምባሳደሯን ከጠራች በኋላ በሞቃዲሾ የሚገኙትንም የኬንያ አምባሳደር ለምክክር አገራቸው እንዲሄዱ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ በሶማሊያ የውስጥና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጣልቃ ገብተዋል የሚለውን ጉዳይ አጣጥተለውታል።
በኬንያና በሶማሊያ መካከል ያለው ግንኙነት በአመታት ውስጥ መሻከር አሳይቷል።
ይህም በህንድ ውቅያኖስ ላይ የሚገኘው በተፈጥሮ ነዳጅና ዘይት የበለፀገው 150 ሺህ ካሬ ሜትር የሚሸፍነው ቦታ እሰጣገባ ጋር በተያያዘ ነው።












