ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በናይጄሪያ በደረሰ አሰቃቂ ጥቃት በርካታ አርሶ አደሮች ተገደሉ
በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ በደረሰ አሰቃቂ ጥቃት ቢያንስ 43 አርሶ አደሮች ተገድለዋል።
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት "ዘግናኝ" ባሉት በዚህ ጥቃት በሩዝ እርሻ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በስለት ታርደው የተገደሉት በትናንትናው (ቅዳሜ) እለት ነው።
ጥቃት አድራሾቹ አርሶ አደሮቹን በቦርኖ ግዛት ማይዱጉሪ በምትባል አካባቢ አስረውም ነው ያረዷቸው ተብሏል።
ቦኮ ሃራምና የምዕራብ አፍሪካው አይ ኤስ ቡድን በከፍተኛ ሁኔታ ይንቀሳቀሱበታል በሚባለው በዚህ አካባቢም በቅርብ ወራት ውስጥ የደረሰ አስከፊ ጥቃትም እንደሆነ ተገልጿል።
እስካሁን ድረስም ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።
"በቦርኖ ግዛት ቀን ተሌት ሳይሉ ኑሯቸውን በሚገፉ አርሶ አደሮች ላይ በአሸባሪዎች የተፈፀመውን ግድያ አወግዛለሁ። እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት ግድያም መላ ህዝቡን አሳዝኗል። በዚህ ጥቃት ቤተሰቦቻቸውን ላጡት መፅናናትን እየተመኘሁ የሟቾችንም ነፍስ በሰላም ያሳርፍ" በማለት ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ተናግረዋል።
"እስካሁን ባለው የ43 ሰዎችን አስከሬን አግኝተናል። ሁሉም ታርደው ነው የተገደሉት። ከዚህም በተጨማሪ ስድስት ሰዎችም ክፉኛ ቆስለዋል" በማለት አርሶ አደሮቹን በማስመለጥ እርዳታ ያደረገ የአካባቢ ታጣቂ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግሯል።
ከዚህም በተጨማሪ ቢያንስ ስድስት አርሶ አደሮች ታፍነው ተወስደዋል ተብሏል።
ጥቃት የደረሰባቸው አብዘኛዎቹ የመጡት ሶኮቶ ከሚባል፣ 1 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ካለው አካባቢ ሲሆን ቦርኖ ግዛትም ለስራ እንደመጡ ኤኤፍፒ ሌላ የአካባቢውን ታጣቂ ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
አርሶ አደሮቹ "ጥቃት የደረሰባቸው ሲያሰቃያቸው የነበረን የቦኮ ሃራም ታጣቂ በቁጥጥር ስር በማዋልና ትጥቁንም በማስፈታታቸው ነው" በማለት የአካባቢው የፓርላማ አባል አህመድ ሳቶሚ ፕሪምየም ታይምስ ለተሰኘ ጋዜጣ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደምም ለሰራዊቱ መረጃን ያስተላልፋሉ በሚል ጥርጣሬ አርሶ አደሮቹ በቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ጥቃት ይደርስባቸው እንደነበር ተዘግቧል።
በባለፈው ወር በመስኖ ስራ የተሰማሩ 22 አርሶ አደሮች በቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ተገድለዋል።
በዛሬው ዕለትም በቦርኖ ግዛት ስድስት ወታደሮች በአድፍጦ ታጣቂዎች መገደላቸውን የቢቢሲው ክሪስ ኤዎኮር ከአቡጃ ዘግቧል።
ወታደሮቹ በግጭት በተፈናቀሉ አካባቢዎች የምግብ ስርጭት ጣቢያን ደህንነት ለመቆጣጠር የተሰማሩ እንደሆነም ተገልጿል።