ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና በአውስትራሊያ ወይን ላይ ከ200% በላይ ቀረጥ ጣለች
ቻይና ከአውስትራሊያ ወደ አገሯ በሚገባ የወይን መጠጥ ምርት ከዛሬ ጀምሮ እስከ 212 በመቶ የሚደርስ ቀረጥ ጣለች።
የንግድ ሚኒስትሩ እንዳሉት ውሳኔው ጊዜያዊ ሲሆን ድጎማ የተደረገበት የአውስታራሊያን ወይን ግዢ ለማስቆም የተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።
ከ107 በመቶ እስከ 212 በመቶ የሚደርሰው ይህ ቀረጥ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ውጥረት የበለጠ ያከረዋል ተብሏል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ቤይጂንግ በፖለቲካ ውጥረቶች ምክንያት ከአውስትራሊያ በሚገቡ እንደ ድንጋይ ከሰል፣ ስኳር፣ ገብስ እና የዓሳ አይነቶችን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን ዒላማ አድርጋ እርምጃ እየወሰደች ነው።
የቻይና ባለሥልጣናት እንደሚሉት አንዳንድ የአውስትራሊያ ወይኖች በድጎማ ምክንያት በቻይና ገበያ ውስጥ በርካሽ እየተሸጡ ነው ሲሉ ይከራከራሉ። አውስትራሊያ ግን ይህንን አስተባብላለች።
የአውስትራሊያ የወይን ገበያ ትልቁ መዳረሻ ቻይና ስትሆን በ2020 የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት ከሽያጩ 39 በመቶውን ድርሻ እንደምትይዝም 'ዋይን አውስትራሊያ' አስታወቋል።
ከአውስትራሊያ ያነሰ ነው በተባለው ዋጋ በቻይና ገበያ የሚሸጡ ወይኖችን በተመለከተ ቻይና ለአንድ ዓመት ምርመራ እያካሄደች ነው።
ዓርብ ዕለት ውሳኔው ይፋ ከተደረገ በኋላ የዓለማችን ትልቁ የወይን አምራች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የትሬዠሪ ዋይን ኤስቴት (ቲደብሊውኢ) የአክሲዮን ዋጋ ከ13 በመቶ በላይ ማሽቆልቆሉን ተመልክቷል።
የቻይና ንግድ ሚኒስቴር እርምጃዎቹ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ አልገለጸም።
የአውስትራሊያ ግብርና ሚኒስትር ዴቪድ ሊትልፕሩድ በትዊተር ገጻቸው ላይ መንግሥታቸው እጅግ በጣም ማዘኑን ገልጸዋል።
"የአውስትራሊያ መንግሥት የወይን ጠጅ አምራቾቻችን ምርታቸውን ቻይና ገበያ ላይ በርካሽ በመጣል ላይ ናቸው የሚለውን ክስ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ያደርገዋል" ብለዋል።
"የአውስትራሊያ ወይን ጠጅ በቻይና እና በመላው ዓለም ባለው ከፍተኛ ጥራት ምክንያት ተወዳጅ ነው። እናም የተሟላ ምርመራ በማድረግም ይህንን ማረጋገጥ እንደሚቻል ሙሉ እምነት አለን" ብለዋል።
የአውስትራሊያ ንግድ ሚኒስትር ሲሞን በርሚንግሃም እንዳሉት አዲሶቹ የቀረጥ ታሪፎች የአውስትራሊያ ወይን በቻይና ተወዳዳሪ እንዳይሆን ና ለገበያ እንዳይቀርብ የሚያደርገ ነው ብለዋል።
ጨምረውም "በቻይና ውስጥ በቅንነት ገበያ ለመሠረቱ ለብዙ መቶዎች የአውስትራሊያ የወይን ጠጅ አምራቾች ይህ በጣም የሚያስጨንቅ ጊዜ ነው" ብለዋል።
ገደቦቹን በተመለከተ ቻይናን በዓለም ንግድ ድርጅት ፊት ለመክሰስ ሀሳብ መኖሩን በርሚንግሃም ጠቁመዋል።
በቻይናና በአውስትራሊያ መካከል ያለው የፖለቲካ ግንኙነት በአስርተ ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛው ከሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን ባለሙያዎች ተናግረዋል።
አውስትራሊያ በሚያዝያ ወር የኮሮናቫይረስ አመጣጥ አንዲጠና ለዓለም አቀፍ ምርመራ ቡድን ድጋፍ የሰጠች ሲሆን፤ ቻይናንም በዋነኝነት ጠቅሳለች ማለታቸውን አንድ ከፍተኛ ዲፕሎማት አስታውቀዋል።
የአውስትራሊያ ምርቶች ከፍተኛ ክትትል እየተደረገባቸው ሲሆን የቻይና ተማሪዎችና ቱሪስቶች ዘረኝነትን በመፍራት ወደ አውስትራሊያ እንዳይጓዙ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።