በቻይና አውስትራሊያዊው ዕጽ በማዘዋወር ወንጀል የሞት ፍርድ ተፈረደበት

በቻይና አውስትራሊያዊው ግለሰብ ዕጽ በማዘዋወር ወንጀል የሞት ፍርድ እንደተላለፈበት የአውስትራሊያ መንግሥት አስታወቀ።

የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙኃን ካርም ወይም ካም ጊሌስፔ ብለው የሚጠሩት ይህ ግለሰብ 7.5 ኪሎ ግራም የሚመዝን 'ሜታምፌታሚን' ወይም 'አይስ' የሚባል ዕጽ በሻንጣው ውስጥ ይዞ በመገኘቱ አየር ማረፊያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር የዋለው ከ7 ዓመታት በፊት እንደነበር ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

ካርም ጊሌስፔ ከጉዋንዡ ደቡባዊ ከተማ በሚገኝ ባዩን አየር ማረፊያ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተነግሯል፡፡

የቻይና መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት በጉዋንዡ በሚገኝ ፍርድ ቤት የሞት ብያኔው የተላለፈበትም ከአራት ቀናት በፊት ነው፡፡

የአውስትራሊያ ውጭ ጉዳይና ንግድ መሥሪያ ቤትም በግለሰቡ ላይ በተላለፈው የሞት ብይን የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡

"አውስትራሊያ በምንም ዓይነት ሁኔታ በማንኛውም ሰው ላይ የሚፈጸም የሞት ፍርድን ትቃወማለች፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሞት ቅጣት መሰረዙን እንደግፋለን፡፡ ይህም ከግብ እንዲደርስ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን" ሲል ባወጣው መግለጫ ላይ አስፍሯል፡፡

ቻይና ምን ያህል የሞት ብያኔ ትሰጣለች?

ቻይና ምን ያህል ሰዎችን በሞት እንደቀጣች መግለጽ አትፈልግም፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ግን በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የሞት ብይኑ እንደሚፈጸም ያምናል፡፡

የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ የሚደረገውም ገዳይ መድሃኒት በመውጋት አሊያም በጥይት ነው፡፡

በርካታ የውጭ አገር ዜጎችም ከዕጽ ዝውውር ወንጀል ጋር በተያያዘ የተገደሉ ሲሆን ሌሎች በርካቶችም የሞት ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡

የሞት ቅጣቱ ከተፈጸመባቸው ግለሰቦች መካከልም ታዋቂው እንግሊዛዊ አክማለ ሻይክህ ይጠቀሳሉ፡፡

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ግለሰቡ የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳለባቸው በመግለጽ ይግባኝ ቢሉም ከ11 ዓመታት በፊት በሞት ተቀጥተዋል፡፡

አውስትራሊያዊያን ላይ ከዕጽ ዝውውር ጋር ተያይዞ እንዲህ ዓይነት ውሳኔም ሲተላለፍ ካርም የመጀመሪያው አይደለም፡፡ከዚህ ቀደምም የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው አውስትራሊያዊያን አሉ፡፡ ከ5 ዓመታት በፊት ዕጽ ሲያዘዋውር በጉዋንዡ አየር ማረፊያ የተያዘው ጋዜጠኛ ቤንጋሊን ሸሪፍ አንዱ ነው፡፡

ይሁን እንጅ ቤንጋሊ በሁለት ዓመታት የእስር ጊዜው መልካም ጠባይ በማሳየቱ የሞት ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ እስራት ተለውጦለታል፡፡

የአውስትራሊያና የቻይና ግንኙነት ከኮሮና በኋላ

የቻይናና አውስትራሊያ ግንኙነት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በንግድ አለመግባባትና የእርስበርስ ወቀሳዎች ሻክሯል፡፡

አውስትራሊያ ባለፈው ዓመት በቻይና ውሃን የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መነሻ ገለልተኛ ወገን እንዲያጣራ ጥሪ ማቅረቧ ቻይናን አስቆጥቷታል፡፡

ቤጂንግም በተደጋጋሚ በእስያዊያን ላይ የሚደርስ ዘረኛ ጥቃቶች እየጨመሩ መሆናቸውን በመግለጽ ዜጎቿ ወደ አውስትራሊያ እንዳይጓዙ አስጠንቅቃለች፡፡ ቻይናዊያን ተማሪዎችም ይህንን የተጋረጠባቸውን አደጋ ከግምት እንዲያስገቡ አሳስባለች፡፡

ከዚህም ባሻገር ቻይና የአውስትራሊያን የበሬ ስጋ ወደ አገሯ እንዳይገባ ያገደች ሲሆን በገብስ ምርቷም ላይ ከፍተኛ ቀረጥ ጥላለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስተር ስኮት ሞሪሰን በበኩላቸው "አውስትራሊያ በቻይና ማስፈራሪያ ፈጽሞ ስጋት አይገባትም" ብለዋል።