ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ፡ ወደ ሱዳን የሚሸሹ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው ተባለ
በፌደራል መንግሥት እና ትግራይ ኃይሎች መካከል የሚደረገውን ጦርነት በመሸሽ ወደ ሱዳን እየገቡ ያሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የሱዳን የስደተኞች ኮሚሽን አስታወቀ።
የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ በግጭት ቀጠናው የቴሌኮም አገልግሎቶች መቋረጣቸው እና መንገዶች ዝግ መሆናቸው የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ለሚያደርገው ጥረት እንቅፋት ሆኖብኛል ብሏል።
በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት ተከትሎ ለወራት በውዝግብ ውስጥ የቆዩት የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል አስተዳደር ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ወደ ግልጽ ጦርነት መግባታቸው ይታወሳል።
የሱዳን የስደተኞች ኮሚሽነር አልሲር ካሊድ ለቢቢሲ በአዋሳኝ የድንበር አቅራቢያ በምትገኘው የሱዳኗ ካሳላ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ እስከ ትናንትናው እለት ድረስ ብቻ ከ5ሺህ በላይ ስደተኞች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አልሲር ካሊድ እንደሚሉት እነዚህ ከ5ሺህ በላይ ስደተኞችን ወደ ሱዳን የገቡት በአንድ በኩል ብቻ ነው።
ኮሚሽነሩ ሉቅዲ ተብላ በምትጠራ ቦታም ትናንት እና ዛሬ 1100 በላይ ስደተኞች መድረሳቸውን ተናግረዋል።
"የስደተኞች ቁጥር ከዚህ በላይ ይሆናል። በአንድ ሳምንት እስከ 20ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ይመጣሉ ብለን እንጠብቃለን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ ምንም እንኳ የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ለስደተኞቹ በቂ ምግብ እና መጠለያ ማቅረብ አለመቻሉን ገልፀዋል።
"በቂ ምግብ እና መጠለያ የለም። መጠለያው እጅግ ትንሽ ነው። 300 ሰዎችን ብቻ ማስተናገድ የሚችል ነው። ያሉት ስደተኞች ግን ከ5ሺህ በላይ ናቸው" በማለት በከሰላ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ያለውን ሁኔታ ይገልጻሉ።
በአካባቢው ከሚሰሩም ሆነ ከሌሎች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እና ተቋማት አጥጋቢ ምላሽ እያገኙ እንዳልሆነ የስደተኞች ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ስደተኞቹ በጣም ተደናግጠው ነው የመጡት። ሦስት እና አራት ቀናት በእግራቸው ተጉዘው ነው እዚህ የሚደርሱት። የጦር አባላት አሉበት፤ በሽተኞችም አሉ" ሲሉ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ሱዳን የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ሊጨምር ይችላል ብሏል።
የተመድ የኢትዮጵያ ተወካይ እና የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ካትሪን ሶርዚ (ዶ/ር) ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ በግጭት ቀጠና የቴሌኮም አገልግሎቶች መቋረጣቸው እና መንገዶች ዝግ መሆናቸው የሰብዓዊ እርዳታ ለማደረግ በሚያደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት እንደሆነበት ገልፀዋል።
ካትሪን (ዶ/ር) በትግራይ ከ800 በላይ የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ የሚሰሩ ሰዎች እንዳሉ ተናግረው፤ "የቴሌኮም አገልግሎቶች ተቋርጠው ይገኛሉ። ይህም በሥራችን ላይ ጫና አሳድሯል። የሰዎች እንቅስቃሴንም መከታተል ከባድ አድርጎታል። የሚያስፈልግ እርዳታ ምን እንደሆነ መለየትም አልተቻለም" ብለዋል።
"ይሁን እንጂ መሠረታዊ የሆኑ እንደ የምግብ እህል ዱቄት እና ነዳጅ እጥረት እንዳለ ሪፖርት ተደርጎልናል። የኤሌክትሪክ አገልግሎትም በተደጋጋሚ ይቋረጣል። ባንኮች ዝግ በመሆናቸው በነዋሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በእኛ ሥራ ላይም እንቅፋት ሆኖብናል" ይላሉ።
የሁመራ፣ ሽሬ እና ሽራሮ ነዋሪዎች በትግራይ ወደሚገኙ ሌሎች ስፋራዎች ስለመፈናቀላቸው ሪፖርት እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
የሱዳን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ከ7ሺህ በላይ ነዋሪዎች ጦርነቱን በመሸሽ ወደ ሱዳን መሸሻቸውን ሪፖርት አድርጓል ሲሉ ካትሪን (ዶ/ር) ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ቀድሞውንም ቢሆን በትግራይ ከ600ሺህ በላይ የሚሆኑ በቋሚነት የምግብ እርዳታ የሚሹ ሰዎች ይገኙ ነበር" ያሉት ካትሪን (ዶ/ር)፤ በአራት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከ96ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች መኖራቸውን ጠቀሰው የሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ለስደተኞቹ የዕርዳታ ድጋፍ የሚሰጠው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ያለው የመሠረታዊ ፍጆታዎች ክምችት በቅርቡ ሊሟጠጥ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ለስደተኞች ቁጥር መጨመር ምክንያት የሆነው ፍጥጫ አሁን ወደ ጦርነት የተሸጋገረው በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መስተዳደር በኩል የነበረው ቅራኔ እየተባባሰ የመጣው ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት እንደማይካሄድ ከታወቀ በኋላ በትግራይ የተናጠል ምርጫ በመደረጉ ሳቢያ ነው።
ይህንንም ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫውን ሕገወጥና ተፈጻሚነት የሌለው እንደሆነ መወሰኑን ተከትሎ ማዕከላዊው መንግሥት ከክልሉ መስተዳደር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያካሂድና የበጀት ድጋፍ እንዳይሰጥ ከወሰነ በኋላ ነገሮች እየተካረሩ መሄዳቸው ይታወሳል።