እንስሳት፡ውሾች የሰው ልጅ እድሜ ጠገብ ወዳጆች መሆናቸውን አንድ ጥናት አመለከተ

ውሾች በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ወዳጅ ሆነው የቆዩ የቤት እንስሳት እንደሆኑና የሚስተካከላቸው ሌላ እንስሳ አለመኖሩን አንድ በቅርቡ የተሰራ ጥናት ጠቁሟል።

በጥናቱ መሰረትም የሰው ልጅ ውሾችን ጓደኛ ማድረግና በቤቱ ማሳደግ የጀመረው ከ11 ሺ ዓመታት በፊት እንደሆነ ተገልጿል።

ይሀም ማለት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደ ውሻ ከሰዎች ጋር አብሮ ለረጅም ዓመታት የኖረ እንስሳ የለም መላት ነው።

ከዛሬ 11 ሺ ዓመታት በፊት ውሾች በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ በኩል በብዛት ይገኙ የነበረ ሲሆን ከዚያም ወደ አምስት አይነት ዝርያዎች ተከፋፍሏል።

ምንም እንኳን በቅኝ ግዛት ዘመን አውሮፓውያን የሚያሳድጓቸው ውሾች ከጊዜ በኋላ ዓለምን ቢወሩም የቀድሞዎቹ አገር በቀል ውሾች ግን አሁንም ድረስ በላቲን አሜሪካ፣ እስያ፣ አፍሪካ እና ኦሽኒያ እንደሚገኙ ጥናቱ ጠቁሟል።

''ውሾች ከሰው ልጅ ጋር እንዴት ወዳጅነት ሊመሰርቱ ቻሉ የሚለው ጥያቄ በጣም አስገራሚ ነው። የሰው ልጅ አደኛና የሜዳ ፍሬዎችን ለቃሚ በነበረበት ጊዜ እንኳን ውሻዎችን አላምዶ ነበር። በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች የውሻ ቤተሰብ የሆነው ተኩላ በጣም አስፈሪና አዳኝ የዱር እንስሳ ነበር'' ይላሉ በጥናቱ ላይ ተባባሪ የሆኑት ዶክተር ፖንተስ ስኮግሉንድ።

''ትልቁ ጥያቄ ሰዎች ለምን ውሻን መረጡ? እንዴትስ ሊሳካላቸው ቻለ? የሚሉትን ጥያቄዎች ነው ለመመለስ የፈለግነው'' በማለት የጥናቱን ዓለማ ያስረዳሉ።

የሆነ ያክል ደረጃ ድረስ የሰው ልጆች ዘረመል እና የውሻዎች ዘረመል አወቃቀር ተቀራራቢ ነው። ምክንያቱም የሰው ልጅ ለመኖር የሄደበት ቦታ በሙሉ አብረው በመሄድ መኖር ስለሚችሉ ነው። ነገር ግን ወሳኝ የሆኑ ልዩነቶችም አሉ።

ለምሳሌ ቀደምት አውሮፓውያን ውሾች የተለያዩ የዘር ሀረጎች ያሏቸው ሲሆን ዋነኛ የዘር ግንዳቸው ግን በሁለት የሚከፈል ነው። የመጀመሪያው ቀረብ ያሉት ምስራቅ አካባቢ ውሻ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሳይቤሪያ ውሾች ናቸው።

ነገር ግን የሆነ ቦታ ላይ አንድ የውሻ ዘር በመላው አውሮፓ የሚገኙ የውሻ ዝርያዎችን በመዋጥ መስፋፋት ችሏል።

ጥናት አድራጊዎቹ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ይኖሩ የነበሩ 27 የውሻ አይነቶችን ቅሪተ አካል በመመርመር ከአሁኖቹ የውሻ ዝርያዎች ጋር ለማመሳከር ጥረት አድርገዋል።

በዚህም መሰረት ለምሳሌ 'ሮዴዢያን ሪጅባክ' የሚባለው በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው እና በሜክሲኮ የሚገኙት 'ቺዋዋ' እና 'ዞሎይትኩንቲ' የውሻ ዝርያዎች ከብዙ ሺ ዓመታት በፊት በአካባቢው ይኖሩ ከነበሩት ቀደምት ውሾች ጋር ዝምድና እንዳላቸው ማወቅ ተችሏል።

ነገር ግን በምስራቅ እስያ የሚገኘው የውሻ ዝርያ እጅግ የተወሳሰበ እንደሆን ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ። በቻይና የሚገኙት የውሻ ዝርያዎች ከዚህ በፊት በአውስትራሊያ እና ኒው ጊኒ አካባቢ ከሚገት ውሾች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው።

በጥናቱ ላይ የተሳተፉት ሌላኛው ተመራማሪ ግሬገር ላርሰን እንደሚሉት ውሾች ከሰው ልጅ ጋር ለብዙ ዓመታት አብረው የቆዩ እንስሳት መሆናቸው የተረጋጋጠ ሲሆን ይህንንም ማድረግ የተቻለው በዘረመል ላይ በተደረገ ጥናት ነው።

ውሾች ከተለያዩ የተኩላ ዝርያዎች የመጡ እንደሆነና የሰው ልጅ አደን በሚያካሂድበት ወቅት ጭምር እገዛ እንደሚያደርጉ ከዚህ በፊትም የሚገመት ነገር ነበር።

በአዲሱ ጥናት መሰረት ደግሞ ሁሉም ውሾች የመጡት ከአንድ በአሁኑ ሰአት ከጠፋ የተኩላ ዝርያ ነው። ነገር ግን ውሾችን ማላመድ መቼና የት ተጀመረ የሚለው እስካሁንም እርግጠኛ ምላሽ ያላገኘ ጥያቄ ነው።

እንደ ድመት ያሉት የቤት እንስሳት ደግሞ የሰው ልጅ ከዛሬ 6 ሺ ዓመታት በፊት በአንድ ቦታ ላይ ተረጋግቶ መኖር ሲጀምር የመጡ ናቸው ተብሏል። ምክንያቱም የሰው ልጅ በአንድ ቦታ ሰፈረ ማለት የሚጥለው ቆሻሻ በሚኖርበት አካባቢ ይጠራቀማል ማለት ነው።

ይህንን ቆሻሻ ተከትለው ደግሞ አይጦች ወደ ሰው ልጅ ሕይወት ገቡ። እነዚህን አይጦች ለማባረርና ለማጥፋት ደግሞ ከድመቶች የተሻለ የቤት እንስሳ የሰው ልጅ አላገኘም።