ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ በአፍሪካ የቫይረሱ ስርጭት ምን ላይ ይገኛል?
የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከያ ተቋም መረጃ እንደሚያሳየው፤ ባለፈው ወር በአፍሪካ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጠነኛ ጭማሬ አሳይቷል።
ሐምሌ አጋማሽ ላይ በየቀኑ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀንሶ ነበር። አሁን ግን እየጨመረ መጥቷል።
በእርግጥ በአንዳንድ አገሮች ቁጥሩ እየቀነሰ ነው።
ባለፉት አራት ሳምንታት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአማካይ 6% መጨመሩን የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከያ ተቋም ገልጿል።
ይህ የታየው ከምዕራብ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ውጪ ባሉ አገሮች ነው።
በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሲቀንስ፤ በግብፅ፣ ኮንጎ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ደግሞ ጨምሯል።
በሴራ ሊዮን፣ ጋምቢያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኢስዋቲኒ እና አይቮሪ ኮስት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል።
የናይጄሪያ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከያ ድርጅት እንደሚለው፤ ቁጥሩ የቀነሰው የሚመረመሩ ሰዎች ስለቀነሱ ሊሆን ይችላል።
የፖሊስ ጭካኔን የሚያወግዙ ሰልፎች ለቀናት መካሄዳቸውን ተከትሎ በአንዳንድ ግዛቶች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል።
የድርጅቱ ኃላፊ ቺክዌ ኢህክዌዙ "ባለፉት ሦስት ሳምንታት ሌጎስ ያለው ቤተ ሙከራችን እንደቀድሞው መሥራት አልቻለም" ብለዋል።
በሌላ በኩል በኬንያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ ነው።
የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከያ ተቋም መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ባለፈው ወር በበሽታው የተያዙ ሰዎች በአማካይ 45 በመቶ ጨምረዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያ ማቲስዲሶ ሞይቲ ኬንያን በተመለከተ "የጥንቃቄ እርምጃዎች ሲላሉ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምር ይጠበቃል። ከቁጥጥር ከመውጣቱ በፊት እርምጃ መውሰድ ይገባል" ብለዋል።
ዜጎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ፣ እጃቸውን አዘውትረው መታጠብ እና አካላዊ ርቀት መጠበቅ ታክቷቸው ሊሆን እንደሚችልም ባለሙያው ያስረዳሉ።
የትኞቹ አገሮች ክፉኛ ተጎዱ?
ደቡብ አፍሪካ በርካታ ሰዎች በበሽታው የተያዙባት እንዲሁም የሞቱባት አገር ናት።
ለሦስት ተከታታይ ወራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቶ፤ አሁን አንድ ነጥብ ላይ ይገኛል። በእርግጥ አንዳንድ ከተሞች ውስጥ ስርጭቱ መስፋት ጀምሯል።
በአንዳንድ ግዛቶች በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የጤና ሚንስትሩ ዝዌንሊ ማክሄዚ አስጠንቅቀዋል።
በበሽታው ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከተመዘገበው በላይ ሊሆን እንደሚችል የደቡብ አፍሪካ የህክምና ጥናት ካውንስል ከወራት በፊት ጠቁሟል።
በግንቦት እና ጥቅምት አጋማሽ መካከል የተመዘገበው የሞት መጠን በ46,759 ጨምሯል።
በአህጉሪቱ የጤና ተቋሞች መሠረተ ልማት ደካማ ቢሆንም በተለያዩ አገሮች የተመዘገበው ሞት ከተቀረው ዓለም አንጻር አነስተኛ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፤ ከ60% በላይ ወየአህጉሪቱ ነዋሪዎች ከ25 ዓመት በታች መሆናቸው ለህልፈት መጠን መቀነስ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
በተጨማሪም ለበሽታው የሚያጋልጡት ከመጠን በላይ ውፍረት እና ስኳር እምብዛም በአፍሪካ አይስተዋሉም።
ሌሎች ወረርሽኞችን በመከላከል የተገኘ ልምድ፣ ከሌሎች የኮሮናቫይረስ አይነቶች የተገኘ በሽታ የመከላከል አቅም እና አነስተኛ የጉዞ ታሪክ የበሽታውን ስርጭት ከቀነሱት መካከል ይጠቀሳሉ።
በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ምን ያህሉ ሕይወታቸው ያልፋል? የሚለው ሲጠና፤ 12 የአፍሪካ አገሮች ከተቀረው ዓለም አንጻር በአማካይ 2.9% ወይም ከዛ በላይ ሆነው ተገኝተዋል።
ምን ያህል ምርመራ እየተደረገ ነው?
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው፤ አሁንም በአፍሪካ የሚደረገው ምርመራ ከሌሎች አህጉሮች ያነሰ ነው።
የድርጅቱ ባለሙያ ማቲስዲሶ ሞይቲ "አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ተጓዦችን፣ ህሙማንን እና ከነሱ ጋር ንክኪ ያላቸውን መመርመር ላይ ነው ያተኮሩት። ስለዚህም በርካታ ያልተመረመሩ ሰዎች አሉ ብለን እንገምታለን" ብለዋል።
በአፍሪካ 75 በመቶ የሚሆነውን ምርመራ ያደረጉት ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ካሜሩን፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ እና ጋና ናቸው።
ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያን ብናነጻጽር፤ ደቡብ አፍሪካ እስከ ጥቅምት 22 ድረስ ከ1,000 ሰዎች 78ቱን መርምራለች። ናይጄሪያ ደግሞ እስከ ጥቅምት 26፤ ከ1,000 ሰዎች ሦስቱን መርምራለች።
በሌላ በኩል በአሜሪካ ከ1,000 ሰዎች 424ቱ፣ በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ 394ቱ ተመርምረዋል።
ከአህጉሪቱ አገሮች ግማሹ ምርመራ እያደረጉ ያሉት የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከያ ተቋም ካስቀመጠው ቁጥር በታች ነው። በአንዳንድ አገሮች ደግሞ ምን ያህል ምርመራ እንደተካሄደ የሚጠቁም በቂ መረጃ አይገኝም።