ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሜክሲኮ ጠፍተዋል የተባሉ የ59 ሰዎች አስከሬን ተገኘ
ሜክሲኮ ውስጥ አብዛኞቹ የወጣቶች የሆኑ 59 አስክሬኖች ስለመቃብር ስፍራነታቸው በማይታወቁ ስፍራዎች መገኘታቸው ተሰምቷል።
በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች አስክሬን የተገኘው በጉዋናሁዋቶ ግዛት ውስጥ ነው።
አስክሬኖቹ የተገኙባት ሳልቫቴራ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእጽ አዘዋዋሪ ቡድኖች አካባቢውን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ፍልሚያ ምክንያት በሜክሲኮ አስፈሪ ከሚባሉት አከባቢዎች መካከል ሆናለች።
በያዝነው ዓመት ብቻ በጉዋናሁዋቶ ግዛት ውስጥ ከ2200 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የተገኙትም አስክሬኖች ከእጽ አዘዋዋሪ ቡድኖቹ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
በሳልቫቴራ ከተማ አስክሬኖቹ ሊገኙ የቻሉት በርካታ ቤተሰቦች የጠፉ ሰዎች ስለመኖራቸው ማስታወቃቸውን ተከትሎ እንደሆነ የሜክሲኮ ብሄራዊ አፋላጊ ኮሚሽን ኃላፊዋ ካርላ ኩዊንታና ገልጸዋል።
ከሟቾቹ መካከል ደግሞ አስር የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑ ኃላፊዋ አክለዋል።
አስክሬኖቹን የማፈላለግ ስራው ላይ ከ80 በላይ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ትክክለኛ ቦታውን አድራሻ ግን ማን እንደሰጠ እስካሁን አልታወቀም።
ነገር ግን ባለስልጣናት ናቸው ምንጩን ሳይጠቅሱ አድራሻውን ለብሄራዊ አፈላላጊ ኮሚቴው ያሳወቁት።
ባለሙያዎቹ በቦታው ከደረሱ በኋ 52 የተለያዩ ቦታዎችን ቆፍረው ነው አስክሬኖቹን ማግኘት የቻሉት ሲሉ ፍለጋው ምን ያክል አስቸጋሪ እንደነበር የፍለጋ ኃላፊው ሄክቶር ዲያዝ ገልጸዋል።
በሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይ ደግሞ በዚሁ ግዛት ውስጥ በሚገኝ የእጽ ሱሰኞች ማገገሚያ ማዕከል ላይ የታጠቁ ሰዎች ባደረሱት ጥቃት 24 ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2018 ላይ ወደ ስልጣን የመጡት የሜክሲኮው ፕሬዝዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ ከእጽ አዘዋዋሪዎች ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመዋጋት ቃል ገብተው ነበር።
ነገር ግን አሁንም በአገሪቱ የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።