ናይጄሪያውያን የሚቃወሙትን ልዩ የፖሊስ ኃይል እንግሊዝ አሰልጥናለች ተባለ

ዘረፋን ለማስቆም የተቋቋመውና ሳርስ ተብሎ የሚጠራውን የናይጄሪያ ልዩ የፌደራል ፖሊስ ኃይል አባላት የእንግሊዝ መንግሥት እንዳሰለጠናቸው የእንግሊዝ የፓርላማ አባል አስታውቀዋል።

ስልጠና ከመስጠትም በተጨማሪ በጦር መሳሪያዎችም እገዛ እንዳስታጠቃቸው በተጨማሪ ይፋ አድርገዋል።

ይህ እገዛም ለአራት አመታት ያህል ቀጥሏል ተብሏል።

የሌበር ፓርቲ ፖለቲከኛዋና የፓርላማ አባሏ ኬት አዛሞር ኦሳሞር በትዊተር ገፃቸው እንዳስታወቁት አገራቸው ከጎሮጎሳውያኑ 2016 ጀምሮ ድጋፍ ያደርግ እንደነበር ነው።

ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን በማሰር፣ ማሰቃየትና ግድያም ይፈፅማል በሚል ከፍተኛ ውግዘት እየቀረበበት ያለውን ልዩ ፖሊስ ተቃውሞ በናይጄሪያ ብቻ ሳይሆን በዩኬና በዲያስፖራ ናይጄሪያውያን አማካኝነት ለሳምንታት ያህል ተካሂዷል።

ፖሊሶች አንድን ሰው ሲገድል የሚያሳይ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎም ነው ተቃውሞቹ የተቀጣጠሉት።

የፖሊስ የጭካኔ በትርን ተቃውመው ከወጡ ሰልፈኞች መካከል 69 ሰዎች መገደላቸውን የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ባለፈው ሳምንት ገልፀው ነበር።

ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበበት ሳርስ እንዲበተን ቢደረግም የሳርስ አባላት በሌሎች የፖሊስ ክፍሎች እየተሰማሩና እየተመደቡ ነው የሚሉ ጉዳዮች መሰማታቸውን ተከትሎም እንደገና ተቃውሞቹ የቀጠሉት።

ሰልፈኞቹ እነዚህ የሳርስ አባላት ለፈፀሙት ወንጀል ህግ ፊት መቅረብ አለባቸውም እያሉ ነው፤ እንዲሁም በአስተዳደሩ ላይ ማሻሻያም ያስፈልጋል እያሉ ነው።

በተለይም ጥቅምት 10/ 2013 ዓ.ም በንግድ ማዕከሏ ሌጎስ በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 12 መድረሱን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ማሳወቁን ተከትሎም ነው ተቃውሞው የተዛመተው።

የናይጄሪያ ጦር በበኩሉ ሪፖርቱ ሃሰተኛ ዜና ነው በማለት አጣጥሎታል።

ከሰሞኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት "ስር ነቀል" የፖሊስ ማሻሻያ እንደሚደረግና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል የተባሉትም የሳርስ አባላት ወደ ፍርድ ይቀርባሉ ብለው ነበር።