ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በናይጄሪያ የፖሊስ ጭካኔን ለመቃወም የወጡ 69 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ
የፖሊስ የጭካኔ በትርን ተቃውመው ከወጡ ሰልፈኞች መካከል 69 ሰዎች መገደላቸውን የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ገልፀዋል።
የሞቱት በርካቶቹ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ቢሆኑም የተወሰኑ ፖሊሶችና ወታደሮችም ይገኙበታል ተብሏል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሳወቁት ከቀድሞ የናይጄሪያ መሪዎች ጋር "መረጋጋት እንዴት እናምጣ" በሚል ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ መሆኑንም ቃለ አቀባያቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተቃውሞ ሰልፉን በዋነኝነት በማደራጀት ላይ ያለው ቡድን ነዋሪዎች ቤታቸው እንዲቀመጡ ጥሪ አስተላልፏል።
የፌሚኒስቶች ጥምረትም እንዲሁ በየግዛቶቹ ያሉትን የሰዓት እላፊ አዋጆችንም አክብሩ ብለዋል።
ምንም እንኳን ተቃውሞዎቹ ቢረጋጉም አሁንም ቢሆን በርካታ ግዛቶች ላይ አለመረጋጋት ይታያል።
በሌጎስ የተላለፈውም የሰዓት እላፊ አዋጅም እንደሚነሳ ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የተጀመረው ተቃውሞ በፖሊሶች አንድን ሰው ሲገድል የሚያሳይ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎም ነው የተቀጣጠሉት።
እነዚህ ተቃውሞዎች በተለይም ዘረፋን ለማስቆም የተቋቋመውን ልዩ የፌደራል ፖሊስ ኃይል ወይም ሳርስ ተብሎ የሚታወቀው ላይ ያነጣጠሩ ሲሆኑ፤ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን ማሰር፣ ማሰቃየትና ግድያም ይፈፅማል በሚልም ከፍተኛ ውግዘትም ቀርቦበታል።
ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበበት ሳርስ እንዲበተን ቢደረግም የሳርስ አባላት በሌሎች የፖሊስ ክፍሎች እየተሰማሩና እየተመደቡ ነው የሚሉ ጉዳዮች መሰማታቸውን ተከትሎም እንደገና ተቃውሞቹ የቀጠሉት።
ሰልፈኞቹ እነዚህ የሳርስ አባላት ለፈፀሙት ወንጀል ህግ ፊት መቅረብ አለባቸውም እያሉ ነው፤ እንዲሁም በአስተዳደሩ ላይ ማሻሻያም ያስፈልጋል እያሉ ነው።
ከሰሞኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት "ስር ነቀል" የፖሊስ ማሻሻያ እንደሚደረግና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል የተባሉትም የሳርስ አባላት ወደ ፍርድ ይቀርባሉ ብለው ነበር።
በተለይም ጥቅምት 10/ 2013 ዓ.ም በንግድ ማዕከሏ ሌጎስ በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 12 መድረሱን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ማሳወቁን ተከትሎም ነው ተቃውሞው የተዛመተው።
የናይጄሪያ ጦር በበኩሉ ሪፖርቱ ሃሰተኛ ዜና ነው በማለት አጣጥሎታል።
የ77 አመቱ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ተቃዋሚዎች የሚያነሷቸውን ትችቶች አስተዳደራቸው እንደሚሰራ ቢጠቅሱም ተቃውሞውን ሽፋን በማድረግ ዘረፋና ሌሎች ህገወጥ ስራዎችን የሚስሩትን ግን መንግሥታቸው እጁን አጣጥፎ አያይም ብለዋል።