ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ህንድ፡በሬሳ ማቀዝቀዣ ውስጥ በህይወት የተገኙት ህንዳዊ ከቀናት በኋላ ሞቱ
በስህተት ሞተዋል ተብለው 'ሬሳቸው' ማቀዝቀዣ ውስጥ እንዲገባ የተደረጉት ህንዳዊ ከቀናት በኋላ ህይወታቸው አልፏል።
ባላስቡራማንያም የተባሉት የ74 አመቱ ህንዳዊ ታሚል ግዛት ውስጥ በሚገኝ የግል ክሊኒክ ውስጥ ሞተዋል ተብለውም የሬሳ ማቀዝቀዣ ውስጥ አስገብተዋቸዋል።
በነገታውም የቀብር ስነ ስርአታቸውን ለመፈፀም ማቀዝቀዣውን ከፍተው በሚያዩበት ወቅት ሰውነታቸው እየተንቀጠቀጠና በህይወት መኖራቸውም ታወቀ።
ሆስፒታል እንደገና ቢወሰዱም ከአምስት ቀናት በኋላ ህይወታቸው እለፏል።
ተመልሰው የተወሰዱበት የመንግሥት ሆስፒታል ኃላፊ ዶክተር ባላጂናታን እንደተናገሩት ህመምተኛው በከፍተኛ ሁኔታ ደክመው እንደነበርና ከሳንባ ጋር በተገናኘ እክልም ህይወታቸው ማለፉን ለቢቢሲ ታሚል ተናግረዋል።
በሬሳ ማቀዝቀዣው ውስጥም ምን ያህል ሰዓታትን እንዳሳለፉ የተገለፀ ነገር የለም።
ሰኞ እለት ሞተዋል ብሎ ዶክተሩ ከተናገረ በኋላ ቤተሰቡ አስከሬኑን ይዘው ወደቤታቸው ከወሰዱ በኋላም በአካባቢው የሚገኝ የጤና ባለሙያም ማቀዝቀዣ እንዲልክላቸው ጠየቁ።
ለወዳጅ፣ ዘመድ አዝማዱም በነገታው የቀብር ስነ ስርአታቸውም እንደሚፈፀም ተነግሮም ነበር።
የቀብር ስነ ስርአት አስፈፃሚ ድርጅቱም የባላስቡራማንያም ወንድም በጤና ባለሙያ የተፈረመ የሞት ሰርቲፊኬት እንዳላቸውም መነገራቸውን አስረድተዋል።
ሆኖም የፖሊስ ኃላፊው ሴንቲል ኩማር እንዳሉት ከሆነ ቤተሰቡ የሞት ሰርቲፊኬቱን ማምጣት አልቻሉም።
ፖሊስም ቤተሰቡ በመጣደፍና ችላ በማለት የሰውን ህይወት አደጋ ላይ ጥለዋል በማለትም ወንጅሏቸዋል።
ግለሰቡ በነርቭ ህመም ችግርም ይሰቃዩ እንደነበር ቤተሰቡ ለፖሊስ ማሳወቃቸውን ኃላፊው አክለው ተናግረዋል።
ባላስቡራማንያም ከባለቤታቸው፣ ሁለት ልጆቻቸውና ወንድማቸው ጋር ይኖሩ ነበር።
በአስከሬን ማቀዝቀዣው ውስጥ ለሰዓታት ያህል በዚያ ቅዝቃዜ ውስጥ በህይወት እንዴት ቆዩ የሚለው ሚስጥራዊ ሆኗል።
ከዚህም በተጨማሪ መጀመሪያ ግለሰቡን ሞቷል ያለው የግል ሆስፒታል እንዲሁም ዶክተር ምርመራ ተከፍቶባቸዋል።