ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፔሩ ሰባት ወር ለጠበቀው ጃፓናዊ ታሪካዊ ስፍራዋን ብቻውን እንዲጎበኝ ፈቀደች
ፔሩ የኢንካ ህዝቦች ስልጣኔ ማሳያ የሆነውን የማቹ ፒቹን ታሪካዊ ስፍራ አንድ ጃፓናዊ ቱሪስት ብቻውን እንዲጎበኝ ክፍት አድርጋለች።
በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከአለም ቅርስ አንዱ የሆነው የማቹ ፒቹ የፍርስራሽ ስፍራ ተዘግቶ የነበረ ሲሆን ጃፓናዊው ቱሪስትም ሰባት ወራት መጠበቅ ነበረበት።
ጄስ ታካያማ ስፍራውን ለመጎብኘት አቅዶ የነበረው መጋቢት ወር ላይ የነበረ ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ጉብኝት በመከልከሉም ሳይሳካለት ቀርቷል።
በቱሪዝም ዘርፉ በርካታ ጎብኝዎች ያሉት ጥንታዊው የኢንካ ከተማ ፍርስራሽ በሚቀጥለው ወርም ላይ በጥቂት ሰዎች ለመክፈት ታቅዷል።
ስፍራው የሚከፈትበት ትክክለኛ ቀን ግን አልተገለፀም።
ጄስ ታካያማ መጋቢት ወር ላይ ወደ ፔሩ ሲመጣ ይህንን ቅርስ ለመጎብኘት የነበረ ቢሆንም በወረርሽኙ ምክንያት መውጣት መግባት ባለመቻሉም በአቅራቢያው ባለች አጉዋስ በተባለች ከተማም ለወራት ያህል ያለ ምንም መሄጃ ጠብቋል።
በዚህም ምክንያት የባህል ሚኒስትሩ አሌሃንድሮ ኔይራ ብቻውን እንዲጎበኝ መፍቀዳቸውን ተናግረዋል።
"ፔሩ የመጣው ስፍራውን የመጎብኘት ህልም ስለነበረው ነው" በማለትም ሚኒስትሩ በትናንትናው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
ጄስ ታካያማ ለሰባት ወር ጠብቆ ስፍራውን ሳይጎበኝ እንዳይመለስ በሚልም ቅዳሜ እለት የፍርስራሽ ስፍራውን እንዲጎበኝ ተደርጓል።
በማቹ ፒቹ ተራራማ ስፍራም ላይ ሆኖ ለወራት የጠበቀውን ቦታ በመጎብኘቱ የተሰማውን ደስታም መግለፁንም በቀረፀው ቪዲዮ አስተላልፏል።
"ጉብኝቱ በጣም አስገራሚ ነበር፤ አመሰግናለሁ" በማለትም ጄስ መልእክቱን አስተላልፏል።
በአንደስ ተራራዎች የሚገኘው የማቹ ፒቹ ስፍራ የኢንካ ግዛት ማሳያ ሲሆን በጎሮጎሳውያኑ 1450 እንደተገነባም ይታመናል።
በዩኔስኮ የአለም ቅርስነት የተመዘገበው ይህ ስፍራ አለም ካላት ሰባቱ አስደናቂ ቅርሶችም ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።
ወረርሽኙ ከተከሰተባት እለት ጀምሮ በፔሩ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 849 ሺህ ሲሆን 33 ሺህ መሞታቸውንም ከጆንስ ሆፕኪንስ የተገኘው መረጃ ያሳያል።