ኢትዮጵያ፡ ተንከባካቢ ለሌላቸው እናቶች መጠጊያ የሆነችው የመቀሌዋ ነዋሪ

በመቀለ ከተማ ተወልዳ ያደገችው አስቴር ገብረታትዮስ መጠለያ የሌላቸውን እናቶች ትንከባከባለች፤ በዚህ የእርጅና እድሜያቸውም መጠጊያ "እሆናችኋለሁ" ብላቸዋለች።

ለዚህ መነሻ የሆናትም በየቀኑ በየጎዳናው ተኝተው የሚለምኑ እናቶችን ያለ መጠለያና ተንከባካቢ ማየት አለመቻሏ ነበር።

በቤተሰብ የእንጨት ስራና ለአመታት የሰራችው አስቴር በካሜራ ሙያ ሰልጥና የራሷንም ፎቶ ቤት ከፍታ ትሰራም ነበር። የእናቶቹ ሁኔታ አንጀቷን ያላስቻለው አስቴር ሙያዋን እርግፍ አድርጋ በመተው እነሱን ለመርዳት ቆርጣም ተነሳች።

በመቀለ ከተማ ውስጥ በተለምዶ 11 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢም ቅዱስ ሚካኤል የአረጋውያን ማደራጃ ማዕከልን ከአራት አመት በፊት አቋቋመች ።

ስትጀምርም በ13 እናቶች ሲሆን ማዕከሉም በአሟቿ ወይዘሮ ጥሩወርቅና ግራዝማች በቀለ ግቢ ውስጥ ይገኛል። ወይዘሮ ጥሩ ወርቅ በህይወት እያሉም መጠለያ ላጡ እናቶች እንክባቤ በመስጠትም ይታወቁ ነበር። አስቴርም ያንኑ ተግባርም ተቀብላ ለአረጋውያኑ የመጨረሻ አመታት ድጋፍ ሆናላቸዋል።

በማዕከሉም ውስጥ ከ70- 110 የእድሜ ባለፀጋ እናቶች ይገኛሉ። በመጀመሪያ አካባቢ ግቢው ውስጥ የገቡ እናቶች በቅጡ እንኳን መጠለያ ያልነበራቸው ሲሆን ከጊዜ በኋላ ግን የአካባቢው ወጣቶች ተሰባስበው ለሁሉም እናቶች መጠለያ የሚሆን ክፍሎችን አስገነቡላቸው።

"እኔ ከቆርቆሮ በተሰራ መጠለያ ውስጥ ነበር እናቶቹን መንከባከብ የጀመርኩት:: ነገር ግን ሳልገልፀው ማለፍ የማልፈልገው በርካታ ሰዎች እንደረዱኝ ነው" ትላለች።

በርካታ ሰዎች ለዚህ በጎ ተግባር የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዳደረጉ የምትናገረው አስቴር ምዕራፍ ካሳ የተባለ ግለሰብ ወጣቶችን በማስተባበርና ገንዘብ በማሰባሰብ፣ የእናት ህክምና ማዕከል ባለቤት ዶ/ር ሳምሶን ሙሉጌታ ለእናቶቹ በሙሉ አልጋና ፍራሽ በመለገስ እንዲሁም ሌሎች ወጣቶች አንሶላ እና ብርድ ልብስ በመለገስ ማዕከሉ እውን እንዲሆን የራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ማህሌት አረጋዊና ቤተልሔም አባይ የተባሉ ነዋሪዎችም ነፃ አገልግሎት በመስጠት ከጎኗ አልተለዩም። የከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ባለቤቷም አቶ አማኑኤል በቀለ ከጎኗ አልተለየም።

"በርካቶችም በየጊዜው ወደ ማእከሉ በመምጣት የእናቶቹን ልብስ ያጥባሉ፣ ፀጉራቸውን ይሰራሉ፣ ጥፍራቸውን ይቆርጣሉ። ከዚያም አልፎ እናቶች በሚታመሙበት ወቅት በመርዳት ያግዙኛል" ስትልም እናቶቹን ለመርዳት እየተደረገ ያለውን የሕብረተሰቡ ትብብር ትገልፃለች።

አስቴር እናቶቹ እንደ ቤተሰብ የሆኗት ሲሆን ሲታመሙም ሆነ በህይወት ሲለዩ ከፍተኛ ኃዘን ውስጥ ትወድቃለች። ማዕከሉን ባቋቋመችበት አራት አመታት ውስጥም አራት እናቶች በሞት መለያታቸውን በጥልቅ ኃዘን ተውጣ ትናገራለች።

በማዕከሉ ከሚኖሩት መካከል ወይዘሮ ሮዚና አፈወርቅ አንዷ ናቸው።

ወይዘሮ ሮዚና ተወልደው ያደጉት አስመራ ነው። አስመራ በነበሩበት ወቅት አነስተኛ ምግብ ቤት ከፍተውም ጥረው ግረው ልጆቻቸውን አሳድገዋል። ያለ መታደል ሆኖ ልጆቻቸውን በሞት ተነጠቁ።

በአሁኑ ጊዜ የመቀለ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሮዚና ከሶስት ግለሰቦችም ጋር እየተዘዋወሩ ምግብ በማዘጋጀት ተቀጥረው ሲሰሩ ነበር። በአንድ መጥፎ ቀንም ወድቀው እግራቸው ተሰበረ፤ ስራ መስራትም አልቻሉም። ደጋፊ፣ ተንከባካቢ በሌላቸውም ወቅት ማዕከሉ አለንልዎት ብሏቸዋል።

"እኔ አስቴርን ደግፏት እንጂ እኔ ደህና ነኝ። እሷን አግዙዋት፤ አይዞሽ በሉዋት: እኛ ከሷ ነው የምንጠብቀው፤ እናንተ ደግሞ እሷን አግዙዋት" ብለዋል ለቢቢሲ

አስቴር ከሰባት ወራት በፊት ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ባደረገችው ቆይታ እናቶቹን ለመንከባከብ ምግብ እንዳጠራትና የሚያግዛት አጥታም ከባድ ችግር ላይ መውደቋን በመጥቀስ ህዝብ እንዲረዳት ተማፅና ነበር።

እናቶቹን መርዳት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከግማሽ ሚልዮን በላይ (560,000) ብር ለማሰባሰብ ችለዋል።

አስቴር በተሰበሰው ገንዘብ አነስተኛ የንግድ ስራ በመስራት ማእከሉ በራሱ እንዲቆምና ያሉትንም ወጪዎች መሸፈን እንዲያስችል እቅድ ይዛለች።