የሴቶች መብት፡ አፍጋናውያን እናቶች በልጆቻቸው መታወቂያ ላይ ስማቸው እንዲሰፍር ተፈቀደ

ከሰሞኑ በአፍጋኒስታን ለሴቶች ስር ነቀል ለውጥ ያሉት ጉዳይ ተከስቷል።

አፍጋናውያን እናቶች በልጆቻቸው መታወቂያ ላይ ስማቸው እንዲሰፍር በህግ ተፈቅዷል።

የአፍጋኒስታኑ ፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ በትናንትናው ዕለት ህጉን በማሻሻል የእናቶች ስም በልጆቻቸው መታወቂያ ላይ እንዲሰፍር አድርገዋል።

በአፍጋኒስታን ህግ መሰረት የልጆች መታወቂያ ላይ የሚሰፍረው የአባቶች ስም ብቻ ነበር።

በአፍጋኒስታን የሴቶች ስም መጠራት እንደ ውርደት ይታያል፤ ሴት ልጅ ስትወለድ ይጀምራል።

እንደ ጨቅላ ወንዶች ዳቦ ተቆርሶ፣ ድግስ ተደግሶ ቀድሞ ስም አይወጣላትም። ዓመታትም ይወስዳል ስሟ እስኪወጣላት ድረስ።

ስታገባም ስሟ በምንም መልኩ አይጠራም። የሠርግ መጥሪያ ካርዱም ላይ ስሟ አይጠቀስም።

እንዲሁ ስትታመመም ስሟ ለሐኪም መነገር የለበትም። በመድኃኒት ማዘዣ ወረቀቱም መስፈሩ የሐጥያት ያህል ይቆጠራል።

በዚህ አያበቃም ህይወቷ ቢያልፍም በሞት ሰርቲፊኬት ላይ ጭራሽ ስሟ አይሰፍርም። ሐውልት ቢሰራም ስሟ አይጠቀስም፤ ባዶ ሐውልት።

በአፍጋኒስታን የሴቶችን ስም በአደባባይ መጥራትም ሆነ ይፋዊ በሆኑ መረጃዎች ላይ ማስገባት ከፍተኛ ነውር ነው።

አንዳንዶችም በህክምና ወቅት ለዶክተሮች ስማቸውን በመንገራቸው ከፍተኛ ድብደባ አጋጥሟቸዋል።

እጃቸውን አጣጥፎ መቀመጥ የከበዳቸው አፍጋኒስታናውያንም 'ስሜ የት አለ' ዘመቻ? ከሶስት አመታት በፊት ጀመሩ።

የዘመቻው መስራችና ጀማሪ የ28 ዓመቷ አፍጋኒስታናዊት ላሌህ ኦስማኒ ስትሆን ዘመቻው መሰረታዊ የሚባለውን በስም የመጠራት መብታቸውን ለሴቶች ለመመለስ ያለመ ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ዘንድ ከፍተኛ ንቅናቄንም የፈጠረው ይህ ዘመቻ ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም የፓርላማ አባላት ድጋፍ አግኝቷል።

በብሄራዊ መታወቂያ ላይ ከአባቶች በተጨማሪ የእናቶች ስም እንዲሰፍርም በከፍተኛ ሁኔታ ጥሪ አድርገዋል።

በማህበራዊ ሚዲያ ጥሪ ሲያደርጉ የነበሩ ሴቶችም የእናቶቻቸውን ስም በፌስቡክ ላይ እያሰፈሩ ነበር። በተገኘውም ድል ላሌህ ኦስማኒ ደስተኛ መሆኗን ለቢቢሲ አፍጋን ተናግራለች።

"የእናቶች ስም እንዲሰፍር በማድረግ ህጉ የተቀየረው ባደረግነው እልህ አስጨራሽ ዘመቻ ነው" ብኣለለች።

በተጨማሪም ለዚህ ዘመቻ ያላሰለሰ ጥረት ያደሩትን አፍጋናውያንን እንዲሁም ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ምስጋናዋን አስተላልፋለች።

ከካቡል የመጡት የፓርላማ አባሏ ማርያም ሳማም "ትግላችን ፍሬ አፍርቷል" በማለት በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።