ሩስያ፡ አሌክሴ የተመረዘባቸው ብልቃጦች ተገኙ

ቭላድሚር ፑቲን በነርቭ ኤጀንት መርዘውታል ተብሎ የሚጠረጠረው አሌክሴ ናቫልኒ እያገገመ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA

ቭላድሚር ፑቲን በነርቭ ኤጀንት መርዘውታል ተብሎ የሚጠረጠረው አሌክሴ ናቫልኒ እያገገመ ይገኛል፡፡

ወደ ሩሲያ ተመልሶ እንደሚሄድም ተወካዩ ተናግሯል፡፡ አሌክሴ የት ነው በትክክል የተመረዘው የሚለው ጉዳይ ሲያወዛግብ ነበር፡፡

እስከዛሬ ይታመን የነበረው አየር ማረፍያ ውስጥ ቡና ከጠጣ በኋላ ነው የታመመው ስለዚህ ቡናው ላይ መርዝ ተጨምሮበት ይሆናል የሚል ነበር፡፡ የሱ ደጋፊዎች ቡድን አሌክሴ የተመረዘባቸውን የፕላስቲክ ብልቃጦች አግኝቻለሁ ብሏል፡፡

አሁን የት እንደተመረዘ አውቀናል፤ አርፎበት የነበረው ሆቴል ውስጥ ነው ብለዋል የሱ ሰዎች በኢኒስታግራም ባሰራጩት መልዕክት፡፡ አሌክሴ ናቫልኒ በሩሲያ ውስጥ ፍርሃት ያልፈጠረበት የፑቲን ተቃዋሚ ሆኖ ነው የሚታየው፡፡

ሙስናዎችን በማጋለጥና የፑቲንን ገመና ለሕዝብ በመዘክዘክ ዝናን አትርፎ ቆይቷል፡፡ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን እውቅ ሆስፒታል ውስጥ ክትትል እየተደረገለት ያለው አሌክሴ አሁን ያለ ዘመናዊ መሣሪያ እርዳታ በራሱ መተንፈስ እንደጀመረ ተነግሯል፡፡

የክሬምሊን ቤት መንግሥት አሌክሴ ስለመመረዙ እኛ የምናውቀው ነገር የለም ብሏል፡፡ በመመረዙ ጉዳይም ምንም አይነት ምርመራ በሩሲያው ውስጥ አልተጀመረም፡፡

ሆኖም የአሌክሴ መመረዝ በበርሊንና በሞስኮ መሀል የዲፕሎማሲ ቅራኔ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ የአውሮፓ ፓርላማ ሐሙስ'ለት በአሌክሴ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ምርመራ እንዲጀመር ሐሳብ አቅርቧል፡፡

አሁን በአሌክሴ የኢኒስታግራም አልበም የተለጠፈ ቪዲዮ እንደሚያሳየው በሰርቢያ ዋና ከተማ ቶክስክ እያለ ያረፈበት ሆቴል ውስጥ የፕላስቲክ የውሀ ብልቃጦች ተገኝተዋል፡፡ እነዚህ ብልቃጦች የተገኙት አሌክሴ መታመሙ ከተሰማ ከሰዓታት በኋላ የሱ ሰዎች የመርዙን መነሻ ለማወቅ ባደረጉት ጥረት ነው፡፡

አሌክሴ በነበረበት ሆቴል ውስጥ በርካታ የውሃ ብልቃጦች (እኛ በተለምዶ የሃይላንድ ላስቲክ የምንላቸው) ተደርድረው ተገኝተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሌክሴ መመረዙ ሲታወቅ በምን እንደተመረዘ የሚገልጽ መረጃ ማግኘት ሕይወቱን ለማትረፍ ወሳኝ ስለነበረ የሱ ሰዎች ይህንኑ ፍለጋ የነበረባቸው ቦታዎችን ሁሉ በፍጥነት አዳርሰዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ አሌክሴ በነበረበት ሆቴል ውስጥ በርካታ የውሃ ብልቃጦች (እኛ በተለምዶ የሃይላንድ ላስቲክ የምንላቸው) ተደርድረው ተገኝተዋል፡፡ ቪዲዮው እነዚህ የውሃ ብልቃጦችን ጓንት የለበሱ ሰዎች ሲሰበስቧቸው ያሳያል፡፡

ኢኒስታግራም አልበሙ ላይ ይህንን ቪዲዮ ተከትሎ የተጻፈው ጽሑፍ እንደሚያትተው በዚህ ክፍል ውስጥ ሳለ በነዚህ ብልቃጦች ውስጥ ነበር መርዙ የተጨመረው፡፡

ሆኖም የሩሲያው ፕሮይክት ዜና አገልግሎት ገጽ ቭላድሚር ኡግሌቭ የተባለ የመርዝ ቀማሚ (ኖቪቾክ መርዝ ከሰሩት አንዱ) በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ አድርጎት ነበር፡፡

ሰውየው እንደሚለው በውሃ ላስቲኮች ውስጥ መርዙ ተቀምጦ ነበር የሚለው የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም መርዙ ውሃ ውስጥ ኖሮ ቢሆን አሌክሴ ዛሬ በሕይወት ሊኖር አይችልም፡፡

መትረፉ የሚያሳየው መርዙ ቆዳውን ብቻ በስሱ መንካቱን ነው፡፡የጀርመን ሐኪሞችም ሆኑ የጀርመን መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ገና አስተያየት አልሰጡም፡፡