ሩሲያ ፡ የጀርመን ሐኪሞች አሌክሴ ላይሞት ይችላል አሉ

አሌክሲ ናቫልኒ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፑቲን እንዳስመረዙት የሚጠረጠረው ተቀናቃኛቸው አሌክሴ ናቫልኒ ወደ ጀርመኑ ዝነኛ ሻርሌት ሆስፒታል ከተዛወረ በኋላ ላይሞት ይችላል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አሌክሴ ከሰርቢያ ጀርመን፣ በርሊን በአውሮፕላን አንቡላንስ ከደረሰ በኋላ ፈጣን ምርመራ ተደርጎለታል።

ሻርለት ሆስፒታል ከምርመራው በኋላ ባወጣው መግለጫ "የላቦራቶሪ ምርመራዎች አሌክሴ ሰውነቱ ውስጥ መርዝነት ያለው ንጥረ ነገር እንዳለ ያረጋግጣሉ" ሲሉ ይፋ አድርጓል።

የመርዙ ዓይነትም "ኮሊነስትራሴ ኢንሂቢተር" ከሚባለው የወል ስም ከሚሰጠው ኬሚካል የሚመደብ ነው ብሏል ሆስፒታሉ።

ሩሲያ አሌክሴን የመረመሩት ሐኪሞች ግን ሰውየው ላይ ምንም ዓይነት መርዛማነት ያለው ነገር አላገኘንም ብለው ነበር።

አሌክሴ ናቫልኒ በጣሙኑ የሚፈሩትንና የማይደፈሩትን ፕሬዝዳንት ፑቲንን በይፋ በመቃወም፣ ሙስናዎችን በማጋለጥ፣ ተቃውሞዎችን በማስተባበር የሚታወቅ ሩሲያዊ ነበር።

አሌክሴ ናቫልኒ ባፈለው ሳምንት ሐሙስ በሩሲያ የአገር ውስጥ በረራ ላይ ሳለ ነበር አውሮፕላን ውስጥ ከፍተኛ የስቃይ ድምጽ ካሰማ በኋላ ተዝለፍልፎ የወደቀው።

ከሳይቤሪያ ቶምስክ ወደ ዋና ከተማ ይበርዋ በነበረው አውሮፕላን ተሳፍሮ የነበረው አሌክሴ ከፍተኛ የስቃይ ጣር ሲያሰማ እንደነበር በግለሰቦች የተቀረጸ ቪዲዮ አረጋግጧል።

ይህንንም ተከትሎ አውሮፕላኑ በድንገት ሳይቤሪያ እንዲያርፍ ከተደረገ በኋላ ወደ ሕክምና ተወስዷል።

አሌክሴ ምናልባት ቶምስክ አየር መንገድ ውስጥ ቁጭ ብሎ ሻይ ሲጠጣ ስለነበር በዚያች አጋጣሚ የሩሲያ ሰላዮች ያዘዘውን ሻይ መርዘውታል የሚል ከፍተኛ ጥርጣሬ አለ።

የተቃዋሚው አሌክሴ መመረዝ ከተሰማ በኋላ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርከልና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አገሮቻቸው ለአሌክሴ ሕክምና ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው በይፋ ገልጸው ነበር።

ሆኖም የሩሲያ መንግሥት በሆስፒታሉ በኩል ሰውየው ወደ አምቡላንስ ለመግባት አቅም የለውም በሚል ሕክምናውን ሲከላከሉ ነበር።

የአሌክሴ ሚስት በበኩሏ የሳይቤሪያው ሆስፒታል ታማሚው ባሏ ወደ ጀርመን እንዳይወሰድ እያዘገየ ያለው ወደሞት አፋፍ ከተጠጋ በኋላ እንደማይተርፈ ሲያውቁ ለመስጠት ነው በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ስታሰማ ነበር።

በመጨረሻ አሌክሴ ወደ በርሊን ሻርለት ሆስፒታል የተወሰደው ቅዳሜ ዕለት ነበር።

ሐኪሞቹ አሁን ተስፋ እንደሰጡት ከሆነ አሌክሴ ሕይወቱ ሊተርፍ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።

የጀርመን ሐኪሞች እንደሚገምቱት ከሆነ ለአሌክሴ የተሰጠው እጅግ አደገኛ መርዝ ነው።

አሁን መርዙን ለማርከስ እየሞከሩ ያሉት አትሮፒን በመስጠት ነው። አትሮፒን እውቅ የመርዝ ማርከሻ ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደም ከዚህ ቀደም የተመረዘው የቀድሞው የኬጂቢ ሰላይ ሰርጌይ ስክሪፓልን ማዳን የተቻለው በዚህ መንገድ ነበር።

አሌክሴ የተመረዘው በምንድነው?

ኮሊኔስትራሴ ኢንሂቢተርስ የኬሚካል አይነት ሲሆን የዚህ ቀንጣት አልዛሚር የተባለውን የመርሳት በሽታን ለማከም ይውላል። በማዳበሪያና በነርቭ ጋዞች ውስጥ አገልግሎት ላይ ሲውል ግን ለሰው ልጅ እጅግ አደገኛ ነው።

ይህ መርዝ ጥቃት የሚያደርሰው ከነርቭ ወደ ጡንቻ የሚሄዱ ወሳኝ ኢንዛይሞችን በመድፈን ነው።

ስለዚህ ይህን መርዝ የወሰደ ሰው ጡንቻዎች አገልግሎት መስጠት፣ መለጠጥም ሆነ መኮማተር ያቆማሉ።

ከዚህም ባሻገር መርዙ የአተነፋፈስ ሥርዓትን ስለሚያዛባ ሰዎች በዚህ መርዝ ሲጠቁ ራሳቸውን ይስታሉ። አሌክሴ የገጠመውም ይኸው ነው ይላሉ ሐኪሞች።