ዜና ማየት ቢቀርብንስ? ሌላው ቢቀር ለአእምሯችን ጤና ስንል!

እኛ ራሳችን ዜና አቅራቢ ሆነን ይህን ማለታችን ወለፈንዲ ሊሆን ይችላል። ትዝብት ላይ ሊጥለንም ይችላል። ያም ሆኖ ግን ነገሩ አሳሳቢ ነው።

ቀኑን ሙሉ የዜና ቆሎ መቆርጠም ቢቀርብንስ? ሌላው ቢቀር ለአእምሯችን ጤና ስንል።

መረጃ ትንፋሽ አሳጣን እኮ፡፡ የመረጃ ሱናሚ ጠራርጎ ወሰደን እኮ…

በኮቪድ ዘመን ደግሞ ቤት ተዘግቶ መዋል የዜና ሸመታችንን ሰማይ አድርሶታል፡፡ በብዙ ዓለም ይህ ነገር እውነት ነው፡፡

እስኪ አስቡት…

እጃችሁ ላይ የቲቪ ትዕይንት መዘርዝር መዘወርያ አለ እንበል፡፡ ሪሞት!

ሌላኛው እጃችሁ ላይ ደግሞ ስልካችሁ ይኖራል፤ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በዚህ ዘመን ከስልካችን ከራቅን ጭንቅ ነው የሚሆንብን፡፡

ምናልባትም ይህን ጽሑፍ በስልካችሁ እያነበባችሁት ይሆናል፡፡

ከንባብ የሚያናጥቡ ተከታታይ መልእክቶች እየደረሷችሁም ይሆናል፡፡ በፌስቡክ…በቴሌግራም…በዋትስአፕ…በትዊተር…

በዚያ ላይ ‹ይቺን አንብባትማ በሞቴ!› የሚለው ሰው ብዛቱ…

"ጉርሻ ይመስል!"

ለምን እንደሆነ ባይታወቅም ሁሉም ሰው የያዘውን ንባብ እንኳ ሳይጨርስ የማጋራት ሱስ አለበት፡፡

አንዳንዱ አጭሬ የቧልት ቪዲዮ ዓይቶ፣ ስቆ እንኳ ሳይጨርስ አጋርቶ ይጨርሳል፡፡ ጊዜ የለም፡፡ የመረጃ ግሽበት አለ፡፡ ስለዚህ ወደሚቀጥለው፡፡ ሳቅን ለማጣጣም ቀርቶ ፈገግታን ለመጨረስ የሚሆን ጊዜ የለም፡፡

እጃችሁ ላይ የቲቪ 'ሪሞት' አለ ብለናል፡፡

ሲኤንኤን፣ አልጀዚራ፣ ቢቢሲ ሰበር ዜና እየላኩ የአእምሮ ጫና ይፈጥራሉ፡፡

ፈነዳ፣ አፈነዳ፣ ፈነዱ….ገደለ፣ ገደሉ…ተገደለ፣ አስገደለ፣ ሞቱ፣ ቆሰሉ…አቆሰለ…ቆሰለ፡፡ ጂኒ ጃንካ ቅብርጥሶ…

ሪሞቱን ይዛችሁታል ብለናል….፡፡ እንዳትለቁት፡፡

ዓለምን በቲቪ መስኮት እየሾፈራችኋት ነው፡፡ በቲቪ የትእይንቶች መዘርዝር ውስጥ 300 ቻናሎች አሉ፡፡ 300 ምርጫዎች አሏችሁ ማለት ነው፡፡

የትኛውን ማየት ይሻላል? ይህ የምርጫ መብዛት ራሱ ለአእምሮ ጤና መልካም አይደለም፡፡

ከቲቪ መዘርዝሩ ጎን የራዲዮ መዘርዝር አለ፡፡ ከሱ ጎን ላፕቶፕ አለ፡፡ ላፕቶፑ ውስጥ እልፍ ፊልሞች አሉበት፡፡

በዚህ ላይ ከጎረቤት የሆነ ራዲዮ ጣቢያው ላንቃው እስኪሰነጠቅ ይጮኻል፡፡ ከወዲያ በኩል ሼልፍ ላይ ያላነበቧችኋቸው መጻሕፍት እያዛጉ ነው፡፡

ዓለም ትጨንቃለች፡፡ መረጃ ይንዠቀዠቃል፡፡ ሰቆቃ…ዜና…ሰቆቃ…መረጃ…ገደሉ፣ ተገደለ፣ ቆሰሉ አቆሰለ፡፡ ጂኒ ጃንካ ቁልቋል….

በዚሁ ሁሉ መሀል ሌላ መልእክት ይመጣል፡፡ ከወዳጅ፣ ከቴሌ፣ ከቴሌግራም ጉጅሌ፣ ከፌስቡክ ክበብ…

መረጃውን እንቀበላለን፤ እንጎርሳለን፡፡ ደግሞ መረጃውን አላምጠን አይደለም የምንጎርሰው፡፡ ምኑ ይላመጥና፡፡ ማስቲካ…ይላመጣል? ይዋጣል? መረጃ ማስቲካ ላንቲካ ሆኗል፡፡ ማመንዠግ ነው እንጂ ሌላ አማራጭ የለም፡፡

ዝምብሎ ማቀበል ነው፣ የሰማው ላልሰማው፡፡ የሰማው ለሰማው፡፡ ወዘተ፡፡

ወዘተ ራሱ ድሮ አጭር ቃል ነበር፡፡ አሁን ወዘተ ረዥም ቃል ሆኗል፡፡

መረጃ ያታክታል፡፡ የዚህ ጽሑፍ እንደ አንጀት መርዘም ራሱ አታካች ነው፡፡ ለምን እዚህ ጋ አናቆመውም፡፡

ምክንያቱም ጸሐፊው ተስፋ ያደርጋላ…ጠቃሚ መረጃ እያቀበለ እንደሆነ ይሰማዋላ፡፡ ስለዚህ አያቆምም ይቀጥላል፡፡ ማንም ደንታው ባይሆንም ይቀጥላል፡፡ ለመረጃ ግሽበት የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት፡፡

በዓይንና ጆሮ የምንሸምተው ዜና ካሎሪ ቢሆን እኮ አለመጠን ወፍረን ፈንድተናል፣ ይሄኔ፡፡ ስኳር፣ ጨጓራ፣ ደም ብዛት፣ ደም ግፊት ነበረብን እኮ ይሄኔ፡፡

ሽንታችን ቀለሙ ቢጫ፣ ሽታው ዜና ዜና የሚል ይሆን ነበር ይሄኔ፡፡

ደግነቱ ዜና ካሎሪ የለውም፡፡ ካሎሪ የለውም ማለት ግን ጭንቅላታችን ላይ አይወጣም ማለት ነው እንዴ? አይደለም፡፡ ልክ እንደ ቢጫ ወባ ዘሎ ጭንቅላታችን ላይ ይወጣል፡፡ ይህን የምንረዳው ግን ዘግይተን ነው፡፡

ፓሮል ጎሽ የ32 ዓመት ወጣት ናት፡፡ በዜና ጎርፍ ተወሰደች፡፡ እንደ ቀልድ ሪሞቱን ታነሳዋለች፡፡ አንዱ ዜና ለሌላው ሲያቀብላት፣ ሌላው ለሌላ ሲያሻግራት እንዲሁ እንደ ቅሪላ እየተለጋች ቀኑ መሽቶ ይነጋል፣ ነግቶ ይመሻል፡፡

‹‹ወንድ ልጅ ቆረጠ፣ ሴት ልጅ ወሰነች›› አልኩ በሆዴ ትላለች ፓሮል፣ የሆነ ቀን፡፡

ፓሮል ቤተሰቦቿ ሕንድ ናቸው፡፡ እሷ ስዊድን ነው የምትኖረው፡፡ ስዊድን ነው የምኖረው ትበል እንጂ እውነተኛ ሕይወቷ ቲቪ ውስጥ ነው፤ ኢንተርኔት ውስጥ ነው፡፡ ስለ ሕንድ አንዱን ዜና ጀምራ ሌላውን ስትገልጥ በሕንድ የወጣች ፀሐይ በስዊድን ትጠልቃለች፡፡

ይህ ሁልጊዜ የሚሆን ነው፡፡ በቀን በቀን፡፡ በመጨረሻ ካሮል ጭንቅላቷ መደንዘዝ ጀመረ፡፡

‹‹ሕንድ እየሆነ ያለው ነገር ቤተሰቤን የሚጨርስ ስለሚመስለኝ ለተደጋጋሚ ጭንቀት ተዳረኩ›› ብላለች ካሮል፣ ለቢቢሲ፡፡

ክሪስ ክላንሲ ደግሞ አለ፡፡ 33 ዓመቱ ነው፡፡ በአውስትራሊያ፣ ቪክቶሪያ ነው የሚኖረው፡፡ የርሱ ሱስ ጫት አይደለም፡፡ ዜና ነው፡፡

ዜና-ሱስ የሚባል ነገር ታሟል፡፡ ዜና ማየት ብቻ አይደለም ችግሩ፡፡ የዓለም ጋዜጠኞችን ልቅም አድርጎ ይከተላል፡፡ በትዊተር፣ በፌስቡክ እግር በእግር ይከተላቸዋል፡፡ አንዲት ቅንጣት ዜና አታልፈውም፡፡ ከዜና በፊት ዜና ያገኛል፡፡

በቀኑ መጨረሻ ግን ይደነዝዛል፡፡ ይታክታል፡፡

ለካንስ ሳያስበው ዓለም ላይ የተፈጠረ ክፉ ነገሮችን በሙሉ በዐይኑ በኩል ሲጠጣቸው ነው የዋለው፡፡

ልክ ማታ ላይ ጭንቅላቱን ሲወቅረው ነው ይህን የሚረዳው፡፡ ቲቪውንና ስልኩን ሲዘጋ ነው የሚታወቀው፡፡

ወደ መኝታው ሲሄድ ሕልሙ ዜና በዜና፡፡ ሽብር በሽብር፡፡

ደግሞ አያስችለውም፣ ጠዋት መልሶ ይከፍተዋል፡፡ ዜናው ደግሞ አይቀየርም፡፡ መልሶ መላልሶ ያው ጉዳይ ይታኘካል፣ ይመነዠጋል፡፡ ማስቲካ ላንቲካ፡፡

‹‹ለጤናዬ ሰጋሁ፤ እየታመምኩ መጣሁ፤ እርምጃ ወሰድኩ፡፡ ዜና በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ማየት ጀመርኩ፡፡›› ይላል ክሪስ ጤናው እንዴት እንደተመለሰለት ሲናገር፡፡

ጎሽ እና ክሪስ ብቻቸውን አይደሉም ይላል ስታትስቲክስ፡፡ ሚሊዮኖች እንደነሱ እየተሰቃዩ ነው፡፡ ምናልባትም ቢሊዮኖች፡፡

ምንም እንኳ በዚህ ክፉ የወረርሽኝ ዘመን ቤት ተዘግቶ መዋል የቲቪ ተጠቃሚዎችን ቁጥር እንዲያሻቅብ ቢያደርግም፤ በብዙ አገራት ግን የዜና ግሽበት ተከስቷል፡፡

ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በከፍተኛ ሁኔታ የተመልካቾቻቸው ቁጥር ቀንሷል፡፡

በአውስራሊያ ደግሞ ከዜና ቻናሎች ይልቅ መዝናኛዎች የተሻለ ተመልካች ቁጥር አስመዝግበዋል፡፡

ፒው የሪሰርች ሴንተር በሰራው አንድ ጥናት ደግሞ በርካታ ሰዎች ስለ ኮሮና ዜና በጭራሽ መስማት አይፈልጉም፡፡ ለምን? አታክቷቸዋላ፡፡

ለምሳሌ በአሜሪካ ከ10 ሰዎች ሰባቱ ስለ ኮሮና ምንም ዓይነት ዜና መስማት ጠላን ብለዋል፡፡

መጥፎ ዜና እንዴት ነው የሚጎዳን?

የአእምሮ ጤና አዋቂዎች ሁለት ነገር ያነሳሉ፡፡

አንዱ የበዛ መረጃ ወደ ታዳሚዎች እየተወነጨፈ የሰዎችን አእምሮ ቀስ በቀስ እየበጠበጠ መሆኑን፡፡ ሁለተኛው ዜና ምን ያህል እንደሚጎዳን አለመገንዘባችን፡፡

ለምሳሌ ስለ ኮሮና ቢጠራቀም አንድ ሜጋ ባይት የሚወጣው ዜና በቀን በቀን ሰምተን ይሆናል፡፡ ግንዛቢያችን ግን በአንድ ኪሎ ባይት እንኳ ጨምሯል? አልጨመረም፡፡

እንደ መረጃው ብዛቱ የመረጃ ጥራት አለን ማለት አይደለም፡፡ የሚመስለን ግን ብዙ በሰማን፣ ባየን፣ ባነበብን ቁጥር ብዙ ማወቃችን ነው፡፡

ለምሳሌ የኮሮና ዜና ዕለታዊ ቢሆንም የሰዎች በበሽታው ላይ ያላቸው ግንዛቤ ግን ተቀራራቢ ነው፡፡ ብዙ ዜና በመስማታቸው ከበሽታው የተፈወሱ የሉም፡፡ ብዙ የዜና እንጀራ በመመገባቸው የተህዋሲውን ክትባት ያገኙ የሉም፡፡

ዛሬ በዚህ አገር እንዲህ ያህል ሰዎች ተያዙ፣ ተመረዙ የሚል ዜና እየወቀረን ስንውል ግን አእምሯችን ላይ ጉዳት እያደረስን ነው፤ እንወቀውም አንወቀውም፡፡

ለምሳሌ ሰዎች ጭምብል ማጥለቅ አለባቸው ተብሏል፣ 2 ሜትር መራራቅ አለባቸው ተብሏል፤ እጃቸውን መታጠብ አለባቸው ተብሏል፡፡ ይህንኑ መረጃ በተለያየ መንገድ ለመቶ ሺ ጊዜ መስማት ትርፉ ምንድነው?

ጆን ፖል ዴቪስ ሳይኮቴራፒስት ናቸው፡፡ ደንበኞቻቸው በመረጃ ሱናሚ ምክንያት ብቻ ለድብታ እና ለጭንቀት እንደተዳረጉ ደርሰውበታል፡፡

ጆን ፖል እንደሚሉት ከሆነ በሌላ የዓለም ጥግ የደረሰ አደጋ በዜና መልክ አእምሯችን ከቀሰመው በኋላ የዘነጋነው ይመስለናል፡፡ አእምሮ ግን ውስብስብ ነው፡፡ ባይታወቀንም የሰማነው መጥፎ ዜና ቀናችንን ያገረጣዋል፡፡

በፌስቡክ ሸርተቴ ሲንሸራተቱ፣ በመረጃ ሲንከላወሱ የሚውሉ ሰዎች አሉታዊነት እንደሚያጠቃቸው ብዙ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ እነሱ የድብታ መጫወቻዎች ነው የሚሆኑት፡፡ ዱካክ ከነ ሠራዊቱ እላያቸው ላይ ይሰፍራል፡፡

ባለማየትና በማየት መሀል ሚዛኑ የቱ ጋ ነው?

ሰዎች ነን፤ የመረጃ ዘመን ላይ ነን፡፡ ያለ መረጃ መኖር አንችል ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መረጃ የአእምሮ ጤናን ያውካል እየተባልን ነው፡፡ ስለዚህ ምን ተሻለ?

ፕሮፌሰር ዴቪስ የአእምሮ ጤና ተመራማሪ ናቸው፡፡ በቀን አንድ ጊዜ ዋና ዋና ዜናዎችን አለፍ አለፍ እያሉ ማየት በቂ ነው ይላሉ፡፡

በዜና ሱስ ለሚሰቃዩ ሰዎች ግን ሚዲያ ቅኝት በሳምንት አንድ ጊዜ በቂ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዴቪስ ሌላው ምክራቸው ዜናን ብቻ ሳይሆን ዜና ጣቢያን ማጋበስ አደገኛ እንደሆነ ነው፡፡

የዜና ምንጫችን ከሚታመኑ አንድ ወይም ሁለት ሚዲያዎች ብቻ ብናደርግ ለአእምሯችን ውለታ ዋልንለት ማለት ነው፡፡

ሚዲያዎች ሁሉ መጥፎ አይደሉም፤ ሁሉም ደግሞ ለጤናዎ በጎ አይደሉም፡፡ በረብ የለሽ የመረጃ ጥይት የማያቆስልዎትን ሚዲያዎች መምረጥ የርስዎ ፋንታ ነው፡፡

አሰስ ገሰሱን የሚያቀርብልዎት ማኅበራዊ ሚዲያ ለአእምሮ መቃወስ ሊዳርግ ይችላል፡፡

ፕሮፌሰር ጆን ፖል ዴቪስ ለሁሉም ነገር ድንበር ማበጀት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡ ለምሳሌ በቀን ውስጥ ጠዋት ወይም ምሳ ሰዓት ላይ አንድ ጊዜ ብቻ ለ15 ደቂቃዎች መረጃ ቃርመን ከዚያ ግን በምንም መልኩ አለመመለስ፡፡

ይህ ግን ይቻላል? እንደሚባለው ቀላል ነው?

በዲጂታል ዓለም ችግሩ የሚጀምረው የመጀመርያዋን ዜና ከማየቱ ላይ ነው፡፡ ከዚያማ እያሳሳቀ ይወስደናል፡፡ በመጨረሻ የጥፋተኝነት ስሜቱ አእምሯችን ይቀውራል፡፡

ምናልባት ራስን በጊዜ የሽቦ አጥር ማጠር አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡

ስልክን አንድ ጊዜ አይቼ እዘጋዋለሁ ብለው የሚከፍቱ የዋሆች ናቸው፡፡ በመረጃ ሱናሚ ተጥረግርገው የማይወሰዱት ስንቶቹ ናቸው?

ፓራል ጎሽ ሰዎችን በሰዓት ገድቦ መረጃን መቆጣጠር እንደሚችሉ መንገር ቀልድ ነው ትላለች፡፡ እሷ ሞክራው አልተሳካላትም፡፡

ለእሷ መፍትሄ የሆነላት መረጃን ከሰዎች አፍ መቀበልን ነው፡፡ ለሻይ ከሰዎች ጋ ስትገናኝ ሰዎች ያወሩላታል፡፡ መረጃ ከአፍ አፋቸው ትቀልባለች፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው መንገድ አልሰራላትም፡፡

አንድ ጊዜ ወደ ስልኬ ከገባሁማ መውጫ የለኝም ትላለች፡፡ የሷ ታሪክ የሚሊዮኖች ታሪክ ነው፡፡

‹‹አሁን ነጻ ወጥቻለሁ፤ በዕለታዊ ቅራቅንቦ ዜና አልታለልም፤ ልቦለድ ማንበብ ነው የምወደው፤ ለሱ ጊዜ በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ ትላለች፡፡››

ይስመርላት!