አሜሪካ፡ ቲክቶክና ማይክሮሶፍት ባለቀ ሰዓት ተፋረሱ

የቲክቶክ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዓለም እጅግ ገናና የሆነው የቲክቶክ ቪዲዮ መተግበርያ ለአሜሪካ ኩባንያ ድርሻውን ለመሸጥ ጫፍ ደርሶ ነበር፡፡ ባለቀ ሰዓት ግን ሽያጩ ከሽፏል፡፡

ቲክቶክ በመጨረሻው ሰዓት ላይ የተፋረሰው ከግዙፉ የአሜሪካ ኩባንያ ከማይክሮሶፍት ጋር ነው፡፡ አሁን ማይክሮሶፍት ከድርድሩ በይፋ የወጣ ሲሆን ቀጣዩ የቲክቶክ ገዢ ኦራክል እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡

ቲክቶክ በአሜሪካ ብቻ 100 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት፡፡ ዶናልድ ትራምፕ እስከ መስከረም 15 ቲክቶክ መተግበሪያውን ለአሜሪካ ኩባንያ ካልሸጠ ይዘጋል ሲሉ መዛታቸው ይታወሳል፡፡

ትራምፕ ቲክቶክ ላይ መራር ፍርድ የሰጡት ኩባንያው የአሜሪካዊያን ዜጎችን መረጃ ለቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ያቀብላል በሚል ነው፡፡

ኩባንያው ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ነህ ከተባለ በኋላ ነው ምርቱን ለመሸጥ የተገደደው፡፡ ቲክቶክ በባለቤትነት የተያዘው በቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ ነው፡፡

ማይክሮሶፍት ቲክቶክን ለመግዛት ጣጣውን እየጨረሰ ነበር፡፡ ባለቀ ሰዓት ትናንት በምን ምክንያት እንደሆነ ባይታወቅም ሽያጩ ተፋርሷል፡፡ ኦራክል የዳታቤዝ ቴክኖሎጂን በመሸጥ በዓለም እውቅ ነው፡፡

ለግዙፍ ቢዝነሶችም የመረጃ ቋት አገልግሎት ያቀርባል፡፡ ዎልስትሪት ጆርናል እና ሮይተርስ ቲክቶክን የሚገዛው ይኸው ኦራክል ድርጅት እንደሆነ አረጋግጠናል ብለው ጽፈዋል፡፡

ኦራክል ቲክቶክን የሚገዛው በሦስት አገራት አገልግሎቱን ለመስጠት ነው፡፡ ከአሜሪካ በተጨማሪ በካናዳ፣ በአውስትራሊያና በኒውዚላንድ፡፡

የቲክቶክ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ በማይክሮሶፍት ግብይት መፋረስ ጉዳይም ሆነ ከኦራክል ጋር ባለው ድርድር ኩባንያው ምንም አስተያየት መስጠት አንፈልግም ብሏል፡፡

ማይክሮሶፍት በበኩሉ ትናንትና እሑድ ባወጣው መግለጫ የቲክቶክ ባለቤት ባይትዳንስ ኩባንያው ቲክቶክን እንደማይሸጥልን አርድቶናል ብሏል፡፡

ትራምፕ ቲክቶክን ከማይክሮሶፍት ይልቅ ኦራክል ኩባንያ እንዲገዛው ውስጥ ውስጡን ፍላጎት አላቸው፡፡ይህም የሆነው የኦራክል ሊቀመንበር ሌሪ ኤሊሰን ወዳጃቸው ስለሆኑ ነው፡፡