አውስትራሊያ፡ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪው ከፖሊስ መኪና ጋር በመጋጨቱ በቁጥጥር ስር ዋለ

ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለው ሜታምፌታሚንስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአውስትራሊያ የአደንዛዥ ዕፅ አፀዋዋሪ ግለሰብ ከቆሙ የሁለት ፖሊሶች ጋር መጋጨቱን ተከትሎ በቁጥጥር ስር ዋለ።

ግለሰቡ ሜታምፌታሚንስ ወይም አይስ ተብሎ የሚታወቀውን አደንዛዥ እፅ በመኪናው ውስጥ ጭኖ ነበር።

ሲሞን ቱ የተባለው ይህ ግለሰብ 260 ኪሎግራም ሜታምፌታሚንስ በመኪናው ውስጥ ይዞ የነበረ ሲሆን ድንገት መኪናውን ሲያዞርም ከፖሊስ መኪኖች ጋር ከአመት በፊት ተጋጭቷል።

ግለሰቡ መኪኖቹን ገጭቶ እየተጣደፈ ለማምለጥ ቢሞክርም ፖሊሶች ተከታትለው በቁጥጥር ስር ያዋሉት ሲሆን መኪናው ውስጥም 95 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት እፅም አግኝተዋል።

ስድስት አመት ተኩልም እስር ተፈርዶበታል።

በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅትም መርማሪው ኢንስፔክተር ግሌን ቤከር ለሪፖርተሮች እንደተናገሩት "ፖሊስ በቀላሉ በአጋጣሚ በቀላሉ እጅ ከፍንጅ የያዘው አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ" ብለውታል

ሲሞን ቱ መኪኖቹን በቆሙበት በገጨበት ወቅት በአንደኛው ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶበት ነበር።

ከገጨ በኋላ ሳያቆም ዝም ብሎ ቢነዳም ሁኔታው በሲሲቲቪ ካሜራ በመቀረፁ እንዲሁም ምስክሮች ስለ መኪናው ዝርዝር መረጃ በመስጠታቸው ፖሊስ በቀላሉ በቁጥጥር ስር ሊያውለው ችሏል።

ከአንድ ሰዓት በኋለም ሲሞን ቱን አግኝተውታል።

ሲሞንም ምግብ እያደረሰ እንደሆነና መኪናውንም አላስፈትሽም በማለት ፀንቶ ነበር።

መኪናው ውስጥ 13 ሳጥን ወይም 260 ኪሎ ግራም ሜታምፌታሚንስ ወይም አይስ ተብሎ የሚጠራውን አደንዛዥ እፅ ይዞ ነበር።

ግለሰቡ ከፍተኛ ዕዳ እንደነበረበትና በየቀኑም የአልኮል መጠጥና ኮኬይንም ይወስድ እንደነበር ተገልጿል።

ዳኛ ፔኑ ሃንኮክ አርብ እለት የእስሩን ብይን አሳልፈዋል። ዳኛው ውሳኔውን ባስተላለፉበትም ወቅት ምንም እንኳን ለጥፋተኛው ግለሰብ መጥፎ አጋጣሚ ቢሆንም ለህዝቡ ግን ጠቃሚ ነው ብለዋል።

ሜታምፌታሚንስ በቅርብ አመታት በአውስትራሊያ ቢቀንስም መንግሥት ግን አደንዛዥ እፁ የሚያደርሰው ጉዳት ከአመት አመት እየጨመረ ነው ብሏል።