እግር ኳስ፡ ዛሬ የሚጀምረውን የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ማን ያሸንፍ ይሆን?

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የ2020/21 እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ፉልሃም ከአርሰናል በሚያደርጉት ጨዋታ 8፡30 ሲል ይጀምራል።

ዛሬ ከሚደረጉ 4 ጨዋታዎች መካከል፣ ያለፈው ዓመት የውድድር ዘመን አሸናፊዎቹ ሊቨርፑሎች፣ ፕሪምየር ሊጉ ከተቀላቀሉት ሊድስ ዩናይትድ ጋር በአንፊልድ የሚያደርጉት ጨዋታ አንዱ ነው።

ማንችስተር ሲቲ፣ ማንችስተር ዩናይትድ፣ ቼልሲና ዎልቭስ ፕሪምየር ሊጉ ከተጠናቀቀ በኋላ በአውሮፓ የውድድር መድረኮች ሲሳተፉ ስለነበር ጨዋታቸውን የሚጀምሩት በሚቀጥለው ሳምንት ነው።

በዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግድ ውድድር ፉልሃም፣ ሊድስ ዩናይትድ እና ዌስት ብሮም አልቢን አዲስ ተሳታፊ ቡድኖች ናቸው።

ሊድስ ዩናይትድ ከ16 ዓመታት ጥበቃ በኋላ ወደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መመለሱን ሲያረጋግጥ፣ ዌስት ብሮም ደግሞ በቻምፒየንሺፕ ውድድር እስከመጨረሻው ጨዋታ ድረስ ጠብቆ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

ፉልሀም ደግሞ በመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ብርንትፎርድን በዌምብሌይ ስታዲየም በማሸነፍ በዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ መሳተፍ የሚያስችላቸው ዕድል አግኝተዋል።

ኖርዊች፣ ዋትፎርድና ቦርንማውዝ ወደ ቻምፒየንሺፑ በመውረድ ከላይ ለተጠቀሱት ሶስት ክለቦች ቦታቸውን የለቀቁ ቡድኖች መሆናቸው ይታወሳል።

ደጋፊዎች ወደ ስታዲም መቼ ይመለሱ ይሆን?

የዘንድሮው የውድድር ዓመት በዝግ ስታዲየሞች የሚጀመር ሲሆን የኮሮናቫይረስ ስርጭትና ሁኔታዎች እየታየ ተመልካቾች ቀስ በቀስ ወደ ስታዲየሞች መግባት እንደሚጀምሩም ተስፋ ተደርጓል።

ምናልባትም የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በዝግ ስታዲየም የሚካሄዱት እስከ ጥቅምት ወር ድረስ ብቻ ሊሆን ይችላል። አርሰናል ከሼፊልድ በኢሚሬትስ በሚያደርጉት ጨዋታ ታዳሚዎች በአነስተኛ ቁጥር ወደ ስታዲየም ሊመለሱ ይችላሉ የሚል ቅድመ ዝግጅት አለ።

እንደውም አንዳንድ ቡድኖች በሙከራ ደረጃ የቅድመ ውድድር ጨዋታዎችና የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታዎች በተመልካቾች ፊት እንዲካሄድና ሁኔታዎች እየታዩ ማስተካከያዎች እንዲደረጉ ሀሳብ አቅርበው ነበር።

አዲስ ፈራሚዎች

በዘንድሮው የዝውውር መስኮት ከፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች እንደ ቼልሲ ድንቅ ተጫዋቾችን የሰበሰበ የለም። ፍራንክ ላምፓርድ እስካሁንም ስድስት ተጫዋቾችን ያስፈረመ ሲሆን ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ ስታንፎርድ ብሪጅ ለማምጣት ቸልሲዎች ደፋ ቀና እያሉ ነው።

የተከላካይ መስመር ተጫዋቹን ቲያጎ ሲልቫ ከፈረንሳዩ ፒኤስጂ፣ የግራ መስመር ተመላላሹ ቢን ቺልዌልን ከሌስተር ሲቲ፣ የአያክሱን የክንፍ መስመር አጥቂ ሃኪም ዚዬክ፣ የአርፒ ሌፕሲዥ የጎል አነፍናፊው ቲሞ ቨርነር፣ የባየር ሊቨርኩሰን የጨዋታ አቀጣጣዩ ኪያ ሃርቭዝ እንዲሁም ወጣቱን ተከላካዩ ማላንግ ሳር ከኒስ አስፈርመዋል።

በዘንድሮው የዝውውር መስኮት በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት ደግሞ ኤቨርተኖች ናቸው። በካርሎ አንቸሎቲ የሚመሩት ኤቨርተኖች አብዱላዬ ዱኩሬን ከዋትፎርድ፣ ሃመስ ሮድሪጌዝን ከሪያል ማድሪድ እንዲሁም አላንን ከናፖሊ አስፈርመዋል።

አርሰናል እስካሁን የሊሉን ተከላካይ ጋብሪኤል ማጋሊያስ እንዲሁም የቼልሲውን ዊሊያን ያስፈረመ ሲሆን ማንቸስተር ዩናይትዶች ደግሞ የአያክሱን የመሃል ሜዳ ተጫዋች ቫን ደ ቢክን አስፈርመዋል።

ማን በበላይነት ያጠናቅቃል?

የዘንድሮውን የውድድር ዓመት የትኛው ቡድን በአሸናፊነት ያጠናቅቃል የሚለው ጥያቄ ደግሞ የዘርፉ ባለሙያዎችን ለሁለት ከፍሏል። አንደኛው ጎራ ሊቨርፑሎች በድጋሚ ሻምፒዮን ይሆናሉ ሲል በሌላኛው ጎራ ደግሞ ዘንድሮ ማንቸስትር ሲቲዎች የሚያቆማቸው የለም ይላሉ።

በርካታ አቋማሪ ድርጅቶች ግን ዘንድሮ ማንቸስተር ሲቲ እንደሚያሸንፍ ግምታቸውን እያስቀመጡ ነው። ነገር ግን የሲቲዎች ደካማ የተከላካይ መስመር ብዙ ጎሎችን የሚያስተናግድ ከሆነ አሁንም ለሊቨርፑል ዋንጫውን አሳለፈው ሊሰጡ እንደሚችሉ ተገምቷል።

ሊቨርፑሎችም ቢሆኑ በዘንድሮው የዝውውር መስኮት ቡድኑን ሊቀይር የሚችል ተጫዋች እስካሁን አለማስፈረማቸው ጨዋታዎቻቸውን ከባድ ሊያደርግባቸው እንደሚችል ባለሙያዎቹ አስጠንቅቀዋል።

በተጨማሪም ቡድኖች ከዚህ በኋላ ለሊቨርፑል የሚሆን አይነት አጨዋወት ይዘው እንደሚመጡ መገመት አይከብድም።

ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቼልሲ ደግሞ ቡድናቸውን በማጠናከር ስራ ላይ እንደመሆናቸው መጠን ከአንድ እስከ አራት ውስጥ ይጨርሳሉ አይጨርሱም የሚለው እንጂ የሊጉ ሻምፒዮን እንደማይሆኑ ግልጽ ነው ብለዋል አቋማሪዎቹ ድርጅቶች።

አርሰናል፣ ቶተንሃም፣ ሌስተር ሲቲና ኤቨርተን ደግሞ ከአምስተኛ በታች ያለውን ቦታ ይዘው እንደሚጨርሱ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።