በትግራይ ምርጫ መራጮች ድምጽ መስጠት ጀመሩ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
የትግራይ ክልል እያካሄደ በሚገኘው ክልላዊ ምርጫ ዛሬ ከንጋት ጀምሮ መራጮች ድምጽ መስጠት ጀምረዋል።
መራጮች ከንጋት 12፡00 ጀምሮ በ2ሺህ 672 የምርጫ ጣቢያዎች ድምጻቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።
መቀለ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ መራጮች ድምጻቸውን ለመስጠት ከንጋት 10፡30 ጀምሮ ምርጫ ጣቢያዎች ፊት ለፊት ተሰልፈው መመልከቱን ገልፆልናል።
በክልሉ 38 የምርጫ ክልሎች እንዳሉ የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል።
በክልላዊ ምርጫው ክልሉን የሚያስተዳድረውን ህወሓትን ጨምሮ 5 ፓርቲዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ በነሐሴ መጨረሻ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ከተላለፈ በኋላ፤ በትግራይ በተናጠል እየተካሄደ የሚገኘው ክልላዊ ምርጫ ሕገ-ወጥና ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት የፌደሬሽን ምክር ቤት መወሰኑ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድም ትናንት ምሽት በኢቢሲ በተላለፈው ቃለ መጠይቃቸው ምርጫው ሕጋዊ አይደለም ብለዋል።
"ሕጋዊ አይደለም [ክልላዊ ምርጫው]። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ምርጫ ማከናወን የሚችለው የምርጫ ቦርድ ብቻ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲረዱት የምፈልገው ነገር ህውሓት ክልሉን ለዓመታት አስተዳድሯል። ክልሉን የማስተዳደር ስልጣኑም እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ እንዲራዘም ተደርጓል ብለዋል።
"አሁን በዚህ ሰዓት የሚደረጉ የእቁብ ስብስቦች ወይም ጉባኤዎች የእኛ ትልቅ እራስ ምታት መሆን የለባቸውም" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ።
"በእኔ በኩል ለኢትዮጵያ ውጊያ ያስልጋል ብዬ አላምንም። እኔ በፍጹም ውጊያ ከሚደግፉ ሰዎች ጎን መመደብ አልፈልግም። እኔ የምፈልገው ለትግራይ አንድ ጥይት መላክ ሳይሆን አንድ የኮሮና አፈ መሸነኛ መላክ ነው የምፈልገው" ሲሉ ተናግረዋል።














