እስራኤል-ዩኤኢ፡ ታሪካዊ በተባለው በረራ ከእስራኤል የተነሳው አውሮፕላን አቡ ዳቢ ገባ

ታሪካዊ በተባለው በረራ ከእስራኤል የተነሳው የመንገደኞች አውሮፕላን ዛሬ ከሰዓት ላይ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ (ዩኤኢ) ደርሷል።

ይህም በእስራኤል እና ዩኤኢ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ትልቁ ምዕራፍ ነው ተብሎለታል።

ኤል አአይ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን የእስራኤል እና አሜሪካ ልዑካን አባላትን ጭኖ የሳዑዲ አረቢያ አየር ክልልን አቋርጦ ከሶስት ሰዓታት በረራ በኋላ የዩኤኢ ምድር ላይ አርፏል።

የበረራ ቁጥር ኤልዋይ971- የዩኤኢን ዓለም አቀፍ የስልክ መጥሪያ ኮድ እንዲወክል በተደረገው በረራ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ ባልና የፕሬዝደንቱ ከፍተኛ አማካሪ የሆነው ጃሬድ ኩሽነር እና የእስራኤል ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሜይር ቤን-ሻባት ይዞ በኤሚሬትስ መዲና አቡ ዳቢ አርፏል።

ጃሬድ ኩሽነር አቡ ዳቢ ሲደርሱ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት ፈር ቀዳጅ ነው ያሉ ሲሆን፤ “ሶስቱ ታላላቅ መሪዎች ለመካከለኛው ምስራቅ አዲስ ምዕራፍ ጽፈዋል። መሪዎቹ የቀጠናው የወደፊት እጣ በኋላኛው ታሪክ መቃኘት የለበትም ብለዋል” ሲሉ የትራምፕ አማካሪው ኩሽነር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ከአረብ ኤሜሬትስ ወደ እስራኤል የሚደረገው በረራ ደግሞ ኤልዋይ972 የሚል በረራ ቁጥር የሚሰጠው ሲሆን 972 የእስራኤል ዓለም አቀፍ የስልክ ኮድን ይወክላል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም የሳዑዲ አረቢያ አየር ክልል ለእስራኤል አየር መንገዶች ዝግ ነበር።

የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በፈረንጆቹ 1948 ለተመሰረተችው እስራኤል እውቅና ስትሰጥ ሶስተኛዋ የአረብ አገር ሆናለች።

ቅዳሜ ዕለት ዩኤኢ ለእስራኤል እውቅና የማይሰጠውን ሕጓን የሻረች ሲሆን ከሳምንታት በፊት ደግሞ በሁለቱ አገራት መካከል የስልክ ግነኙነት እንዲጀመር ፈቅዳለች።

በእስራኤል እና በአረብ ኤምሬትስ መካከል ያለው ግንኙነት የተለሳለሰው በአሜሪካ አሸማግይነት ሲሆን፤ ነሐሴ 13 ነበር ወዳጅነታቸውን ይፋ ያደረጉት።

በአብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ይህ ዜና በመልካም ቢወሰድም፤ ፍልስጤም ግን ተቃውሞዋን ገልጻለች። በተለይም የአረብ ኤምሬትስ ለፍልስጤም እውቅና ካልሰጠችው እስራኤል ጋር ግንኙነት መፍጠራቸው፤ ፍልስጤምን መክዳት ነው ተብሏል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ከአረብ ኤምሬትስ ጋር ዳግመኛ መወዳጀታቸውን አስታከው በወረራ የተያዘውን ዌስት ባንክ በግዳጅ የእስራኤል ይዞታ የማድረግ እቅዳቸውን ለማዘግየት ተስማምተዋል።