ኮሮናቫይረስ ፡ በኢትዮጵያ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ለማስጀመር መመሪያ ተዘጋጀ

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን መልሶ ለማስጀመር የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ እንዳለው የወረርሽኙ ስጋት ባለበት ሁኔታ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መልሰው እንዲጀመሩ ለማድረግ በተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

የአገሪቱ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ኤሊያስ ሽኩር እንደተናገሩት በበሽታው ምክንያት የተቋረጡትን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከዚህ በላይ እንዲዘገዩ ማድረግ በስፖርት ቤተሰቡ ላይ የሚፈጠረው ጫና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር ሲባል በአገሪቱ ስፖርታዊ ስልጠናዎች፣ ውድድሮች በአጠቃላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ተደርጎ ቆይቷል።

በዚህም ሳቢያ የስፖርት ዘርፍ ክፉኛ መጎዳቱን ያመለከተው ኮሚሽኑ፤ ክለቦች የመፍረስ አዳጋ እንደተጋረጠባቸውና የስፖርት ቤተሰቡም የሥነ ልቦና እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ መግባታቸውን ገልጿል።

በመሆኑም አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ ረቂቅ መመሪያው ተዘጋጅቶ ውይይት ተካሂዷል።

መመሪያው አጠቃላይ የስፖርት እንቅስቃሴዎች በምን ሁኔታ መከናወን እንዳለባቸው የሚያሳይ ሲሆን የስፖርት ተቋማትና ማኅበራት ከሚያካሂዷቸው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ባህሪ አንጻር አስፈላጊ የጥንቃቄና የአሠራር ሥርዓት ሊያዘጋጁ እንደሚችሉ እንደሚያመለክት ኮሚሽኑ ገልጿል።

በዚህም መሰረት የስልጠናና የውድድር ስፍራዎች ለበሽታው ያላቸውን ተጋላጭነት ባገናዘበ ሁኔታ ደረጃ በደረጃ በግልና በቡድን አነስተኛ ተሳታፊ ቁጥርን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ ተቀምጧል።

እንዲሁም ወደ ስልጠናና ወድድር የሚገቡ አካላት ምርመራ ማድረግ፣ የንጽህና መጠበቂያዎችን መጠቀምና ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያገለግሉ ቦታዎች፣ ቁሳቁሶችና መሳሪያዎች ንጽህናቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ መመሪያው ጠቅሷል።

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ውድድርን መልሶ ለማስጀመር እየታሰበ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ውድድሩ ሲጀመር የተመልካቹንና የስፖርተኞቹን ጤና ደኅንነት ያስጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለማከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ከታወቀ በኋላ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑና በርካታ ሰው የሚታደምባቸው ስፖርታዊ ውድድሮችን የመሰሉ እንቅስቃሴዎች እንዳይካሄዱ መደረጉ ይታወሳል።