ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ፡ ፖሊሶች ጄኮብ ብሌክ ላይ መተኮሳቸውን በመቃወም ቴኒስ ተጫዋቿ ኦሳካ ራሷን ከውድድር አገለለች
ጃፓናዊቷ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ናዮሚ ኦሳካ ፖሊሶች ጄኮብ ብሌክ ላይ መተኮሳቸውን በመቃወም ከታላቁ የኒው ዮርክ ቴኒስ ውድድር ራሷን አገለለች።
“ጥቁር ሴት እንደመሆኔ እኔ ቴኒስ ስጫወት ከማየት በበለጠ ቅድሚያ የሚሰጣቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች እንዳሉ አምናለሁ” ብላለች በትዊተር ገጿ።
ምንም መሣሪያ ያልታጠቀው ጥቁር አሜሪካዊው ጄኮብ ላይ ፖሊሶች ከጀርባው ተኩሰውበታል።
እሁድ በኪኖሻ ግዛት ከተተኮሰበት በኋላ በመላው ዊስኮንሰን ተቃውሞ ተቀጣጥሏል።
በፖርትላንድ፣ ሚኒሶታና ሌሎችም ግዛቶች ተቃውሞው ቀጥሏል።
ከወራት በፊት ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ መገደሉን በመቃወም በመላው አገሪቱ የ ‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ [የጥቁሮች ሕይወት ዋጋ አላት] ሰልፎች መካሄዳቸው አይዘነጋም።
ደብሊውቲኤ የተባለው የሜዳ ቴኒስ ውድድር አዘጋጆች እስከ አርብ ድረስ ጨዋታው እንደተሰረዘ አስታውቀዋል።
“የዘር መድልዎና ኢፍትሐዊነትን የቴኒስ ስፓርት እንደሚቃወም ማሳየት እንፈልጋለን” የሚል መግለጫም አውጥተዋል።
ናዮሚ ኦሳካ ከግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ መውጣቷን መግለጿን ተከትሎ ነበር ይህ መግለጫ የወጣው።
በጃፓንኛና በእንግሊዘኛ በጻፈችው ትዊት “ቴኒስ ስላልተጫወትኩ ትልቅ ነገር ይፈጠራል ብዬ አልጠብቅም። ነገር ግን ነጭ ተጫዋቾች በሚበዙበት ስፖርት ውስጥ አንዳች ውይይት እንዲጀመር ምክንያት ከሆንኩኝ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ እየተራመድን ነው” ብላለች።
ናዮሚ አያይዛም “ጥቁሮች በፖሊሶች እየተገደሉ መሆኑን ሳይ ያመኛል” ስትል ሀዘኗን ገልጻለች።
ጃፓናዊና የሄይቲ ውህድ የሆነችው ናዮሚ፤ ጃፓን ውስጥ የዘረኝነት ሰለባ ናት።
ማስታወቂያዎች ላይ የቆዳ ቀለሟን ሲያነጡ፤ ቆዳዋን ነጭ ማድርግ አለባት እያሉ የሚሳለቁ ኮሜዲያኖችም አሉ።
በስፓርቱ ዓለም ጄኮብ ብሌክ ላይ መተኮሱን የተቃወሙ ሌሎችም አሉ። የቅርጫት ኳስ ቡድኑ ሚልዋኪ ባክስ ከውድድር መውጣታቸውን ተከትሎ ኤንቢኤ ሦስት ግጥሚያዎች ሰርዟል።
ሁለት የቤዝቦል ጨዋታዎችም ተሰርዘዋል።
ፖሊሶች ጄኮብ ላይ የተኮሱት ያሳለፍነው እሁድ ሦስት ልጆቹ ወደ ነበሩበት መኪና ሲገባ ነው።
አሁን ሆስፒታል ውስጥ እያገገመ ሲሆን፤ ጠበቃው ከዚህ በኋላ መራመድ ከቻለ ተዓምር ነው ብለዋል።
ፖሊሶች ጄኮብ ላይ ሰባት ጊዜ መተኮሳቸውን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።