ትራምፕ፡ "ጆ ባይደን ከእኔ ጋር ክርክር ከመግጠምህ በፊት የአበረታች መድኃኒር ምርመራ አድርግ"

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ "ጆ ባይደን ከኔ ጋር ክርክር ከመግጠምህ በፊት ኮሮና ተመርመር" ሲሉ ተደምጠዋል።

በመጪው ምርጫ ይፋለማሉ ተብለው የሚጠበቁት ትራምፕና ባይደን በቀጣዩ ወር ክርክር ሊያደርጉ ቀጠሮ ይዘዋል።

ዋሽንግተን ኤክዛሚነር ከተባለ ጣቢያ ጋር ቆይታ የነበራቸው ትራምፕ ጆ ባይደን አቅማቸው ጎልበት ብዬ አይቸዋለሁ። መድኃኒት እየተጠቀሙ ሳይሆን አይቀርም ሲሉ ተደምጠዋል።

ትራምፕ ተቀናቃኛቸው መድኃኒት እየተጠቀሙ እንደሆነ መገመታቸውን ይናገሩ እንጂ ምንም ማስረጃ አላቀረቡም።

እንዴት እርግጠኛ ሆኑ? ተብለው የተጠየቁት ዶናልድ፤ "እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር በማስተዋል የተካንኩ ነኝ" የሚል ምላሽ ነው የሰጡት።

ትራምፕና ጆ ኅዳር ላይ ከሚካሄደው የአሜሪካ ምርጫ በፊት ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ክርክር ይገጥማሉ።

ዶናልድ፤ ባለፈው ምርጫ ተቀናቃኛቸው የነበሩት ሂላሪ ክሊንተን ወደ ክርክር ከመምጣታቸው በፊት የሆነ አነቃቂ ነገር ይወስዳሉ፤ ይመርመሩልኝ ማለታቸው አይዘነጋም።

የሂላሪ ክሊንተን ሰዎች በወቅቱ የትራምፕን ወቀሳ ውሃ የማያነሳ ሲሉ አጣጥለውት ነበር።

ዕለተ ረቡዕ ቃለ መጠይቅ የነበራቸው ዶናልድ ለአሁኑ ተቀናቃኛቸውም ተመሳሳይ ጥሪ አቅርበዋል - 'እውነተኛ ነኝ ካልክ ተመርምረህ ና' የሚል።

ትራምፕ፤ የቀድሞው ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከዚህ ቀደም ቴሌቪዥን መስኮት ላይ ሲቀርቡ 'ቃላት የማይታዘዟቸው ነበሩ'፤ አሁን ግን ነቃ ነቃ ብለዋል ይላሉ።

ፕሬዝደንቱ ተቃናቃኛቸው ጆ የዴሞክራት ፓርቲ ዕጩ ሆነው ከመቅረባቸው በፊት ከበርኒ ሳንደርስ ጋር በነበራቸው ክርክር ላይ 'ደርሰው እሳት የላሱ' መሆናቸው አልጣማቸውም።

"ዕጩ ከመሆናቸው በፊት በነበሩ መድረኮች ላይ አቅም አልባ ሆነው ነበር የታዩት፤ ድንገት ከበርኒ ጋር በነበረው ክርክር ላይ ጎልብተው መታየታቸው እንዴት ሊሆን እንደቻለ አላውቅም' ብለዋል ፕሬዝደንቱ።

"ክርክሩ እኮ ደባሪና እንዲሁ ፈዛዛ ነበረ። ምንም የተለየ ነገር አልታየበትም" ሲሉ የሁለቱን ዴሞክራቶች ክርክር አጣጥለውታል።

"እኛ የአበረታች መድኃኒት ምርመራ እንዲካሄድ ጥሪ እናቀርባለን እንጂ ዝም ብለን አናይም።"

ትራምፕ በሳቸውና በተፎካካሪያቸው ጆ ባይደን መካከል የሚደረገው ክርክር የሞት የሽረት እንደሚሆን ይናገራሉ።

"ትግሉ ቀላል አይሆንም። እኛ አፋችንና ጭንቅላታችንን ነው የምንጠቀመው። ደግሞ ቆመን ነው የምንከራከረው። እኔ ሁሉም እንዲቆም እፈልጋለሁ - እነሱ መቀመጠ ነው የሚፈልጉት።"

የመጀመሪያ ክርክር ክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ ውስጥ መስከረም ወር መገባደጃ ላይ ይደረጋል። ሁለተኛ ደግሞ በፍሎሪዳዋ ማያሚ ጥቅምት አጋማሽ ላይ ቀጠሮ ተይዞለታል። የመጨረሻው ክርክር ወርሃ ጥቅም ሲገባደድ ናሽቪል ቴኔሲ ውስጥ የሚደረግ ይሆናል።

ትራምፕ ከጆ ባይደን ጋር አንድ ተጨማሪ ክርክር እንዲኖራቸው ቢጠይቁም የፕሬዝደንቶች ክርክር ኮሚሽን ጥያቀያቸውን ውድቅ አድርጎታል።

የመጀመሪያ ክርክር ቀደም ብለው ለሚመርጡ ሰዎች ሲባል ከተያዘለት ቀጠሮ ቀድሞ ይካሄድ ብለው ጠይቀው ነበር ፕሬዝደንቱ። ኮሚሽኑ ይህንንም ውድቅ አድርጎታል።

የ74 ዓመቱ ትራምፕና የ77 ዓመቱ ጆ ባይደን 'የአእምሮ ሕመም አለብህ' ተባብለው ተሰዳድበው ያውቃሉ።